መጪው ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን የላቀ ተሳትፎ ማረጋገጥ አለበት- ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
መጪው ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን የላቀ ተሳትፎ ማረጋገጥ አለበት- ፌዴሬሽኑ
አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 መጪው ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን በአግባቡ እንዲያሳትፍ የዝግጅት ስራ ካሁኑ መጀመር እንዳለበት ተጠቆመ።
ያለፉት አገራዊም ይሁን የማሟያ ምርጫዎች አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊ ከማድረግ አንፃር ክፍተት የታየባቸው እንደነበሩ ነው የተጠቀሰው።
"በመጪው ምርጫ አካል ጉዳተኞችን ማካተት" በሚል መሪ ሐሳብ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ውይይቱን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ከፊንላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የምርጫ ስርዓቶች በመራጭነትም ይሁን በተመራጭነት አካል ጉዳተኞችን ከማሳተፍ አንጻር ውሱንነቶች ነበረባቸው።
ከምርጫው ቅስቀሳ አንስቶ እስከ ምርጫ እለት ያሉት ሂደቶች የአካል ጉዳት ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ አላደረጉም።
ለአብነትም ከመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳቸውን ሲሰሩ የአካል ጉዳተኞችን ሲቀሰቅሱ አልታዩም፤ በምርጫ ጊዜም የምርጫ ቦታዎቹ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ካለመሆናቸው በተጨማሪ አካል ጉዳተኛው በቂ መረጃ ኖሮት በምስጢራዊነት ምርጫውን እንዲፈፅም የሚያስችሉ አልነበሩም ነው ያሉት።
ከዚህም ሌላ አካል ጉዳተኞች የመመረጥ መብት በህገመንግስቱ የተሰጣቸው ቢሆንም ተመራጭ ሆነው እንዲቀርቡ ከማድረግ አንፃር ሰፊ ክፍተት አለ ብለዋል።
በዚህም አገር ለመምራት አቅሙ ያላቸው አካል ጉዳተኞች የአመራርነት ድርሻ እንዳይኖራቸው ማድረጉን አስረድተዋል።
የምርጫ ቦታ ለመድረስ ለዊልቼር አመቺ አለመሆን፣ በገለጻ ወቅት የምልክት ቋንቋ አለመጠቀም፣ ማየት ለተሳናቸው የብሬል መምረጫ አለመኖር የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ባለፈው ምርጫ የተጀማመሩ ነገሮች ቢኖሩም በይድረስ ይድረስ የተሰሩ ስለነበሩ ውጤታማ አለመሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ከዚህ አንጻር ፌደሬሽኑ ከፊንላንድ መንግስት ጋር በመሆን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመወያየት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ችግሩን ለመፍታትም ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ግንዛቤውን የማስፋት ስራ መጀመሩን ነግረውናል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ለአካል ጉዳተኞች ከነበረው የግንዛቤ እጥረት ምክንያት መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራም አነስተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
በመጪው ምርጫ ታዲያ ይህ ችግር እንዲፈታ ካሁኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የምርጫ ስርዓቱና ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች የሚያስፈልጉ ነገሮችን የሚያሟሉ እንዲሆኑ ከምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።