ቀጥታ፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ለስልጠና ወደ ኳታር አምርታለች

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ለስልጠና ወደ ኳታር አቅንታለች።

ሊዲያ በፈረንሳይ አስተናጋጅነት ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ስምንተኛው የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ እንድታጫውት ህዳር 2011 ዓ.ም በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(ፊፋ) መመረጧ የሚታወስ ነው።

ለዓለም ዋንጫው ቅድመ ዝግጅት በኳታር ርዕስ መዲና ዶሃ በሚካሄደው የኢንተርናሽናል ዳኞች ሴሚናር ላይ ለመሳተፍ ሊዲያ ትናንት ሌሊት 7 ሰዓት ላይ ወደ ስፍራው ማቅናቷን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ በኳታር በሚኖራት ቆይታ የተሻሻሉ የዳኝነት ህጎች እና በሴቶች ዓለም ዋንጫ የሚተገበሩ ህጎችን ስልጠና እንደምትወስድ ተገልጿል።

ከስልጠናው በተጨማሪ ሊዲያ በኳታር በሚካሄድ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች ውድድር በዳኝነት እንደምትመራም ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

በኳታር የሚሰጠው ስልጠና ፊፋ በዓለም ዋንጫው የተመረጡት ዳኞች ብቁ ሆነው በመቅረብ ጨዋታዎችን በብቃት መምራት እንዲመሩ የተዘጋጀ መሆኑን ፊፋ ገልጿል።

በቀጣይም ለዳኞቹ ተከታታይ የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል።

የፊፋ የዳኞች ኮሚቴ በፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ እንዲያጫውቱ 27 ዋና ዳኞችና 48 ረዳት ዳኞችን የመረጠ ሲሆን ዳኞቹ ከ42 አገራት የተውጣጡ ናቸው።

በዚሁ መሰረት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በውድድሩ በመሐል ዳኝነት እንዲመሩ ከተመረጡት ሶስት የአፍሪካ ዳኞች መካከል አንዷ ሆናለች።

ዛምቢያዊቷ ሌንግዌ ግላዲስና ሩዋንዳዊቷ ሙካንሳንጋ ሳሊማ ከአፍሪካ የዓለም ዋንጫን እንዲያጫውቱ የተመረጡ ሌሎች ዳኞች ናቸው።

ሁሉም ዳኞች የተመረጡት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ባሳዩት ወቅታዊ ብቃት መሰረት ነው።

ሊዲያ በጋና አስተናጋጅነት ከህዳር 8 እስከ ህዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው 11ኛው የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ጋና ከአልጄሪያ ያደረጉትን የመክፈቻ ጨዋታ እንዲሁም ናይጄሪያ ከካሜሮን ያደረጉትን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት መምራቷ ይታወሳል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2015 በካናዳ በተካሄደው ስድስተኛው የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ የተካሄዱ ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት የመራች ሲሆን የፈረንሳዩ ዓለም ዋንጫ በውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ እንድታጫውት ያደርጋታል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ እና የዮርዳኖስ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ፣ በ2018 የፈረንሳይ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫና ሌሎች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የተካሄዱ የማጣሪያ ውድድሮችን በብቃት መምራት ችላለች።

በፈረንሳይ በሚካሄደው የሴቶች የዓለም ዋንጫ የአውሮፓ አህጉር ዘጠኝ ዳኞችን በማስመረጥ ቀዳሚው ሲሆን የኦሺኒያ አካባቢ አንድ ዳኛ ብቻ አስመርጧል።

አፍሪካ በዓለም ዋንጫው በናይጄሪያ፣ ካሜሮንና ደቡብ አፍሪካ ትወከላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም