ቀጥታ፡

የተቋማት ቅንጅት መጓደል ወጣቶች በሚፈለገው ልክ ወደ ስራ እንዳይገቡ አድርጓል-ኤጀንሲው

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖርና በቂ ድጋፍና ክትትል አለመደረጉ ወጣቶች  በሚፈለገው ልክ ወደ ስራ እንዳይገቡ   እንቅፋት መሆኑን የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም አብሮ ለመስራት ዝግጁ ቢሆኑም ከእቅድ ጀምሮ መነጋገር በመካከላቸው ባለመኖሩ አብሮ መስራቱ ፈተና ሆኖብናል ይላል። 

በአገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች 75 በመቶ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ የስራ ዕድል ለመፍጠር "እየሰራሁ ነው" የሚለው ኤጀንሲው ከዚህ ውስጥ እስካሁን 60 በመቶውን ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ ነው የሚገልጸው።

በኤጀንሲው  የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ፈረደ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ቅንጅታዊ አሰራር የለም ይላሉ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ  በበኩላቸው ቅንጅታዊ አሰራሩ እንዳይተገበርም ትልቁ ፈተና አስቀድሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያስፈልጋቸው ባለማስታውቃቸው ነው ይላሉ።

መላኩ አክለውም "ለኃይል ግብዓትነት የምንጠቀምባቸውን መሳሪያዎች በውጭ ምንዛሬ የምናስገባ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር ነው፤ ሆኖም  መንግስት ለዘርፉ የሚሰጠውን ትኩረት ተፈጻሚ ለማድረግ እንሰራለን ይላሉ። ነገር ግን ቅንጅታዊ አሰራሩ መኖር ያለበት ከእቅድ ጀምሮ መሆኑን በማውሳት።

በመሆኑም ተደራሽነታችን ውስን በመሆኑና በርካታ ደንበኞች አዳዲስ ኃይል ለማግኘት እየተጠባበቁ ስለሚገኙ፣ ለወጣቶቹ መስሪያና መሸጫ ቦታዎች ሲዘጋጁ ያለንን የኃይል ኃብት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለማሰራጨት  ደንበኞቹ አስቀድሞ የማሳወቅ ሁኔታ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ሌላኛው የአገልግሎት ሰጪ ተቋም የሆነው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንን በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ምላሽ ባለማግኘቱ  አልተሳካም።

በኤጀንሲው በኩል በጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎትና በንግድና በመሳሰሉት የስራ ዕድል የሚፈጠር ሲሆን ፤ በአገሪቷ ለስራ አጥ ዜጎች ከሚፈጠሩት የስራ ዕድሎች ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ ለወጣቶች የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተሰራበት ያለውም ጉዳይ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መሆኑን የኤጀንሲው ዳይሬክተር ገልጸው፤ የተጠናከረ ስራ ለመስራት በዚህ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር የተቋቋመ ኮሚሽን መኖሩንም ተናግረዋል።

ለአብነትም ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ለወጣቶቸ የስራ ፈጠራ የተሰጠው 2 ቢሊዮን የተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቱ እየተሰጠ ላለው ትኩረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፡ በቀጣይም በክልል ከተሞች ሄደቱ እንደሚቀጥል አቶ አሰፋ አክለዋል።

ኤጀንሲው በአገር አቀፍ ደረጃ በተያዘው ዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን ለመፍጠር በእቅድ እየተንቃሳቀሰ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም