በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ተደረገ

125

ጎንደር  መጋቢት 19/2011የደብረታቦር ከተማ የንግዱ ማህበረሰብና የጢስ አባይ ከተማ ወጣቶች ግማሽ ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የምግብና አልባሳት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ።

የንግዱ ማህበረሰብ ተወካይ የአቶ ማስረሻ ለተፈናቃዮቹ  የተሰበሰበ 400 ኩንታል በቆሎ ፣  400 የሕጻናትና የአዋቂዎች አልባሳትን  በመጠለያው ተገኝተው  አስረክበዋል፡፡

ድጋፉን ካስረከቡ በኋላም "ተፈናቃዮቹ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው የሰው እጅ እያዩ መቀመጣቸው ልብ የሚነካና ነገ ዛሬ ሳንል በዜግነታችን ፈጥነን ልንደርስላቸውና ልንደግፋቸው ይገባል" ብለዋል

የጢስ አባይ ከተማ  ተወካይ አቶ   ጌታቸው አጥናፉ በበኩላቸው የከተማው ወጣቶችና ነጋዴዎች  ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል ስሜት በመነሳሳት 176 ኩንታል በቆሎ አሰባስበው ለተፈናቃዮች እንዲሰጥ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ተመልስው እስኪቋቋሙ ድረስም  ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም  ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ባንቲሁን መኮንን ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ እንደተናገሩት የክልሉ ህዝብ ለተፈናቃዮች የሚያደርገው ድጋፍ ቀጥሏል።

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በመንግስት የታቀደው መርሃ ግብር እንዲሳካ ህዝቡ ከዕለት እርዳታ ባሻገር ለቤት መሰሪያ የሚውል የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ተሳትፎውን እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዞኑ ከ58 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በ13 ጊዚያዊ መጠለያዎችና ከወዳጅ ዘመድ ጋር እንደሚኖሩ ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም