ቀጥታ፡

ለውጡ ያመጣቸውን የሐሳብ ብዝሀነትና የዴሞክራሲ ምህዳር ትሩፋቶችን የሚመራ አቅም አልተገነባም --- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 ባለፈው አንድ ዓመት የመጣው ለውጥ የሐሳብ ብዝሀነትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እድል ቢሰጥም ለውጡን መምራት የሚያስችል አቅም አለመገንባቱ ተገልጿል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኤዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን እንዳሉት ባለፈው አንድ አመት በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና የሀሳብ ብዝሀነት ለማስተናገድ እድል ቢሰጥም ይህን መምራት የሚያስችል አቅም በህዝብም ሆነ በመንግስት ተቋም ደረጃ አለመገንባቱን ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት“በለውጡ እስረኞች ተፈተዋል፤ በሽብርተኝነት ተመዝግበው የነበሩ ሰዎች ወደ ሀገር ገብተዋል፤ መገናኛ ብዙሃን ነጻነት ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ ነገር በራሱ የሀገሪቱን ችግር ይፈታል ባይባልም ተስፋ አሳይቷል” ነው ያሉት።

ከለውጡ በፊት የተለየ ሀሳብ ማራመድና ብሄራዊ እርቅን ማንቋሸሽ በተቃዋሚዎችም ሆነ በኢህአዴግ የነበረ ተግባርን የቀየረና ሰላምን ማስፈን ዓላማው ያደረገ የሰላም ሚኒስቴር በመንግስት መቋቋሙ ጥሩ ጅምር እንደሆነ የጠቀሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት  አቶ ተሻለ ሰብሮ  ናቸው።     

“ኢትዮጵያዊነትን ክልላዊነት እየዋጠው ነው የሚለው ጥያቄያችን ሰሚ አግኝቶ የለውጥ አመራሩ ኢትዮጵያዊነትን እያቀነቀነ ነው” ይላሉ።

የኢህአዴግ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ፤ ኢህአዴግ ከለውጡ በፊት የነበሩበትን በርካታ ችግሮች   በጥልቅ ተሃድሶ ገምግሞ ወደ ለውጥ መግባቱን ነው የገለጹት።

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን  ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት መምህር   ዶክተር ሀይለሚካኤል ሙሌ እንደሚሉት በአሁኑ ሰአት ለሁሉም ነገር  መሪዎቻችን መልስ ይስጡን የሚል እምነት  መፈጠሩ የመንግስትን ቅቡልነት ቢያሳይም ሁሉም በየደረጃው የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ በግለሰብ ላይ ብቻ መጫኑ፤ መሪው ለስትራቴጂክ ጉዳዮች ትኩረት እንዳይሰጥ ጫና ይፈጥራል።   

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንዳሉት ባለፈው አንድ ዓመት የመጣው  ለውጥ ህዝቡ ተስፋ ባደረገበት መንገድ ስኬታማ እንዲሆን አመራሮች ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ መውሰድ ባለመቻላቸው፤ ግለሰቦች ለለውጡ ቢሰሩም መዋቅራዊ ለውጥ  ያለመኖር በየደረጃው ያሉ አመራሮች አቅምም ሆነ ተነሻስነት ውስን መሆኑ ኢህአዴግ ለውጡን መምራት አለመቻሉን ያሳያል ነው ያሉት።

“ለውጡ ከመስቀለኛ መንገድ ቢያወጣንም አሁን ደግሞ ወደ ገመድ ጉተታ ገብተናል፤ የለውጥ ሃይሎቹ ከብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ ጫፍ ሆነው ወደ ዴሞክራሲ፣ ወደ ልማት፣ ወደ ተሻለች ሀገር ይጎትታሉ፤ ሌላው ሃይል ደግሞ በተቃራኒው እየጎተተ ነው ” ያሉት አቶ ተሻለ ሰብሮ  ናቸው።

የመፈናቀል፣ የመገፋፋትና የዘረኝነት ፖለቲካ ለለውጡ ስጋት መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።

የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተገኙ ውጤት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና ተቀዛቅዞ የነበረው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ የተደረገው ጥረት ለውጡን በመምራት የመጣ ውጤት መሆኑን በማሳያነት የሚጠቅሱት ደግሞ የኢህአዴግ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ  አቶ ሳዳት ነሻ ናቸው፡፡

ለውጡ በተፈለገው ፍጥነት ላለመሄዱ ለብዙ ግዜ የተከማቹ ችግሮችን በአንድ አመት መፍታት እንደማይቻልና ለውጡን መምራት የሚያስችል አቅም በየደረጃው አለመፈጠሩንም ሃላፊው አስረድተዋል።  

ለውጥ  በታቀደና በድንገት መከሰት ባህሪው መሆኑና  በኢትዮጵያም ለውጥ በህዝባዊ ተቃውሞ በመከሰቱ  ለተወሰነ ግዜ አለመረጋጋት መታየቱ ተፈጥሮአዊ  እንደሆነ  ነው ዶክተር ሀይለ ሚካኤል ያነሱት፡፡

መንግስት የህዝቡን የኢኮኖሚ፣ የስራ አጥነት፣ የመዋቅር ና የፍትህ ጥያቄዎችን ለመመለስ የለውጡን አቅጣጫ ከማስቀመጡ  በፊት  የሀገርን ሰላም ማስፈን ቅድሚያ እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።  

ኢህአዴግ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትንና ችግሮችን በዘለላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ያሉት አቶ ሳዳት በውሥጥም ሆነ በሌሎች ሀይሎች ከዚህ በተቃርኖ የሚሰሩ አካላትን እንታገላለን ይላሉ፡፡

መንግስት ያለበትን ችግር እንዲቀርፍ መገሰፅና ለህዝብ  አማራጭ አጀንዳ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሌሎች አጀንዳ ውስጥ ተጣብቀዋል የሚሉት   ኢንጅነር ይልቃል በዚህ ምክንያትም አማራጭ የፖለቲካ ሃይል መሆን አልቻሉም ብለዋል፡፡

መንግስት የምርጫ ቦርድን እንደገና ማዋቀሩ፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች  መወያየታቸው  የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ መስራቱን ተፎካካሪ  ፓርቲዎች እድሉን  ተጠቅመው ውጤታማ  ተፎካካሪ  ካልሆኑ  ችግሮችን ሁሉ በመንግስት ማላከክ የትም አያደረስም ያሉት  ደግሞ አቶ ተሻለ ሰብሮ  ናቸው ።

ለውጡን ለማስቀጠል መንግስት በአጭርና በረጅም ግዜ የሚፈታውን ችግር ለህዝቡ ማሳወቁ የተሻለ መተማመን በመፍጠሩ በፍጥነት  ወደ ተግባር መገባት እንዳለበት አቶ ሃይለሚካኤል  ምክራቸውን  ሰጥተዋል።

“ መንግስት መፍትሄ የሚሰጥበትን ግልጽ አቅጣጫ በማስቀመጥ ህዝብ የሚሳተፍበትንና በትዕግስት የሚጠበቅበትን እድል ለመፍጠር መወያየት ያስፈልጋል” ያሉት ዶክተር ሀይለሚካኤል ይህ ባለመሆኑ  መንግስት የሚሰራቸውን ተግባራት ህዝቡ እየተረዳው አይደለም  ብለዋል።  

ችግሩን ለመቅረፍ በየደረጃው ባለው መዋቅር በአጭርና በረጅም ግዜ የሚፈቱበትን መርሀ ግብር በማሳወቅ ግልፅነት መፍጠር ስቻል፤ ህዝቡም እርስ በእርስ በመወያየት ለመፍትሄውም በጋራ  ለመሥራት እድል እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም