ቀጥታ፡

ባለፉት 12 ዓመታት ከ6 ሺ 600 ከተሞች በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ውስጥ በአገሪቷ የሚገኙ ከ6 ሺ 600 በላይ ከተሞች የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። በዚህም በ1997 ዓ.ም ከነበረው የ23 በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን ወደ 58 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፕሮግራም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ለገሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የፕሮግራም ቢሮው በ1997 ዓ.ም ተቋቁሞ በአገሪቷ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል። በዚህ ፕሮግራም ቢሮው በተቋቋመ በ12 ዓመታት ውስጥ የአገሪቷን ገጠራማ አካባቢዎች ጨምሮ ከ6ሺ 600 በላይ ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ይህም በአገሪቷ የነበረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ከነበረበት 23 በመቶ ወደ 58 በመቶ ማድረስ መቻሉን ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። የሽፋን መጠኑ በዚህ ደረጃ እያደገ ይምጣ እንጂ የሚታዩ የሃይል መቆራረጦችና የአሰራር ችግሮች  በተጠቃሚው ህብረተሰብ ዘንድ ቅሬታ የሚያስነሱ ጉዳዮች መሆናቸውንም ተናግረዋል። አገልገሎቱን በዘላቂነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና አሰራሩን ለማዘመን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የኔትወርክ ዝርጋታና የማሻሻያ ስራዎች  እየተሰሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በአሰራሩ ላይ የአቅም ውስንነትና የስራ መጓተቶች  እንዳይኖሩ ለማስቻልም በዘርፉ የተሰማሩ ኮንትራክተሮችንና በጥቃቅን የተደራጁ ማህበራት ተሳታፊ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል። ይህም ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት ከመስራት በዘለለ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይምጣ እንጂ የሚያጋጥሙ የሃይል መቆራረጦች በስራቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱን ተገልጋዮች ያነሳሉ። በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ትራንስፎርሜሮችና ምሰሶዎች ላይ እንዲሁም ማከፋፈያ መስመሮች ላይ የሚያጋጥሙ ብልሽቶች በስፋት የሚስተዋሉ እንደሆነም ነው የሚያነሱት። ወይዘሪት ቡንጉሌ ያደታ በእንጀራ መጋግርና ማከፋፈል የተሰማራች ወጣት ናት ፤ቆጣሪው ሃይል  ስለሌው ቀን ቀን መስራት አይቻልም ፤ አራት ምጣድ አንድ ላይ መስራት አንችልም፤ ስሪ ፌዝ ቆጣሪ  ሃይለኛ ፓወር ያለው ወፍጮ እንኳን ማንቀሳቀስ ይቻላል ተብለን ነው የተሰጠን ግን አሁን ስሪ ፌዝ ከሶስት ምጣድ በላይ ማሰራት አይችልም ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፋንቱ ሞላ በአካባቢያችን ያለው  ፖል አጠገባችን ነው ያለው ሁሌይፈነዳል ፤ግን እግዚዓብሄር ይመስገን ተመልሶ እራሱ ይጠፋል ነው ያሉት ። እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ ከዚህ በፊት የእንጨት ምሰሶዎች ቶሎ የማርጀት፤ የመለዋወጫ እቃ እጥረትና የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ትራንስፎርመር ብልሽት ተግዳሮት ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የማስፋፊያና የምሰሶ ግንባታ ስራዎች በአገሪቷ ዋና ዋና እና ትላልቅ ከተሞች ላይ የማስፋፊያና የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል። እነዚህ  የማስፋፊያና የማሻሻያ ስራዎችም በጥሩ አፈጻጸም ላይ የሚገኙ መሆኑንና ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ የሚታዩ የሃይል መቆራረጦችን በማስቀረት ለተገልጋዮች ቅሬታ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። አሰራሩ በቀጣይም አገልገሎቱን ማግኘት ያልቻሉ  አካባቢዎችን ተደራሽ በማድረግ እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም