ቀጥታ፡

በጎንደር በጎ ፈቃደኞች የለገሱት 6 ሺህ ዩኒት ደም ተጎጂዎችን ታድጓል

ጎንደር መጋቢት 18/2011 በጎ ፈቃደኞች የለገሱት 6 ሺህ ዩኒት ደም ሕይወት መታደጉን የጎንደር ከተማ ደም ባንክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የተሰበሰበው ደም በአካባቢው ለሚገኙ 16 የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች ተሰራጭቷል።

የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ደመቀ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት በጎንደርና አካባቢው ነዋሪዎች፣ መንግሥት ሠራተኞችና ተማሪዎች የተለገሰው ደም  ተጎጂዎችን የታደገው በሆስፒታሎች ተሰራጭቶ ነው፡፡

ባለፉት ስምንት ወራት የተሰበሰበው ደም በግጭት የተጎዱ ወገኖች፣ ወላድ እናቶች፣ የካላዛር ሕሙማንና የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

"በአካባቢው በነበረው ግጭት ምክንያት ደም የሚያስፈልጋቸው ተጎጂዎችና ሕሙማን ቁጥር በመጨመሩ በጽህፈት ቤቱ ከተሰበሰበው በተጨማሪ 220 ዩኒት ደም ከክልልና ከብሄራዊ ደም ባንክ በማስመጣት እንዲሰራጭ ተደርጓል" ብለዋል ።

በዚህ ዓመት የተሰራጨው ደም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ1ሺህ 70 ዩኒት ብልጫ እንዳለው የገለጹት አስተባባሪው፣ ምክንያቱም የኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማደግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጽህፈት ቤቱ ያሉትን 225 መደበኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ለማሳደግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ  አቶ ደመቀ ተናግረዋል ።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሁለተኛ ልጃቸውን የተገላገሉት ወይዘሮ አሰለፍ ማሩ በሰጡት አስተያየት በወሊድ ወቅት ከፍተኛ ደም እንደፈሰሳቸውና ከክፍያ ነፃ በተሰጣቸው ደም ህይወታቸው መትረፉን ገልጸዋል፡፡

"በሆስፒታሉ ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ደም ባይኖር፤ ሕይወቴ አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር" ያሉት ወይዘሮ አሰለፍ፣ ለተደረገላቸው ልገሳ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከመደበኛ ደም ለጋሾች መካከል ወይዘሪት ሙሉ ሀጌ  ለ36 ጊዜ ለግሰዋል።

"ደም በመለገስ ሕይወት ማትረፌ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል" ብለዋል።

ሌሎችም ደም እንዲለግሱበመምከርና በማስተማር ላይ  መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኢንስፔክተር በድሉ ኃይሌ በበኩላቸው "በአደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ በማሰብ ለ13 ጊዜ ደም ደም ለግሻለሁ" ብለዋል ።

ጽህፈት ቤቱ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ 8ሺህ 400 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም