ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ ስጋት ገጥሞናል አሉ

አዲስ አበባ  መጋቢት 18/2011 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጸጥታ ስጋት ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ ስጋት ገጥሞናል አሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንደሚሉት በአገሪቷ  የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሳቢያ እየተሻሻለ የመጣውን  የፖለቲካ ምህዳር በአግባቡ ለመጠቀም አዳጋች ሆኗል።

ኢትዮጵያ በለውጡ ያገኘቻቸውን የህዝብ አንድነትና መረጋጋት የመጠቀም ሰፊ ዕድል ቢኖራትም በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን ማስቆም ባለመቻሉ ፓርቲዎች  በነጻነት ለመንቀሰቀስ ተቸግረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ  ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት በተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ መልካም ጅምሮች ታይተዋል እስረኞች ተፈተዋል፣ መገናኛ ብዙሃን ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል፣የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ተደርጓል።

መንግስት በለውጡ እነዚህን መልካም ጀምሮች ያሳየ ቢሆንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አልቻለም ።

በዚህም ሳቢያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመሃል ከተማ ውጪ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ አጀንዳቸውን ለማስተዋወቅና ከደጋፊዎቻቸውና ከአባሎቻቸው ጋር ነጻ ውይይት እንዳያደርጉ ተገድበዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ''መኢአድ'' ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ እንደሚሉት በአገሪቷ በተገኘው ለውጥ የፓርቲያቸውን ዓላማ በነጻነት ለማስተዋወቅ ያለጥያቄ ለመንቀሳቀስ መደላድሎች ተፈጥረዋል።

ይሁንና ፓርቲዎች ከመታሳርና ከመደብደብ ስጋት ነጻ ቢሆኑም በአገሪቷ የሚታዩ የሰላምና መረጋጋት ችግሮች የነገ ህልማቸውን ከወዲሁ እየተፈታተኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፓርቲው አሁን ስለመታሰር ሳይሆን የሚያስበው የሰለጠነ ፖለቲካን ስለማራመድና በሃሳብ ብልጫ በማሸነፍ አገርን የሚጠቅም መሪ ማፍራት ላይ ነውም ብለዋል።

ነገር ግን የተገኘውን ነጻነት በአግባቡ ለመጠቀም የዚህችን አገር ህልውናን እየተፈታታኑ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች በጊዜው መፍታት አለመቻል ስጋት ላይ እንደጣላቸው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በመንግስትና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል ግልጽ የሆነ የማስፈጸሚያ ሰነድና ውይይት  ያስፈልጋል ያሉትየቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው።

መንግስት በግልጽ የራሱን አቋም አስተዋውቆ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዓላማቸውንና ግባቸውን በአግባቡ አስተዋውቀው እየተንቀሳቀሱ አይደለም ብለዋል።

በዚህና በሰላም እጦት ሳቢያ የተጀመረው ለውጥና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በተፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ ገደብ ሊያደርግ ስለሚችል ከወዲሁ መፍትሄ መሰጠት አለበትም ብለዋል። 

እንደ ፓርቲዎቹ ጥቆማ መንግስት በአገሪቷ እየታየ ያለውን የሰላም መደፍረስ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች በመውሰድ ዜጎች ያለስጋት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም