በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር ይገባል - ምሁራን
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2011 በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ የኢኮኖሚ ዘርፉን መምራት የሚችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ።
መንግስት በሀገሪቷ ላይ የሚያደርገውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ (Economic Reform) ምሁራንን በማሳተፍና በበቂ ጥናት መደገፍ እንዳለበትም ገልጸዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማትና ምጣኔ ሃብት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ካሳ ተሻገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከሰባት በመቶ በላይ ነው፤ ይኸውም ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገሮች ጎራ ይመድባታል።
ይሁን እንጂ ዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማምጣት "የኢኮኖሚ ዘርፉን በአግባቡ መምራት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት የለም" ይላሉ።
ኢኮኖሚው በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መምጣት በኋላ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው በመሆኑ መነቃቃት ቢታይበትም ቀጣይነቱ አስተማማኝ እንዲሆን ጠንካራ ተቋማት መመራት እንደሚገባው ገልጸዋል።
ዘላቂ ልማትና እድገት ማምጣት የሚቻለው በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በወጪ ምርቶች ጥራትና እሴት በሚጨምሩ ተቋማት አቅም መጎልበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት መምህርና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ በበኩላቸው የተቋማት አደረጃጀት ያረጁና ለዘመኑ ወጣት የሚመጥኑ ባለመሆኑ በአዲስ አሰራር መተካት አለባቸው ብለዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ጨምሮ የፖለቲካና የማህበራት አስተዳደር ስርዓት በሂደት እየተቀየረ መሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚደረገው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ለውጥ የዘርፉ ምሁራንና የሚመለከታቸውን አካላት ባካተተ ጥልቅ ጥናት መደገፍ እንደሚገባም ያሳስባሉ ዶክተር ብርሃኑ።
መንግስት በሚያደርገው የተቋማት አደረጃጀት ለውጥ ካሁን በፊት እንደነበረው በፖለቲካ ተሳትፎ ሳይሆን በብቃት መሆን እንዳለበትም ዶክተር ካሳ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት እንደነበረውና አሁንም እየሆነ ያለው የሚሰጥ የነበሩ ሹመቶች በግንኙነትና በፖለቲካ ታማኝነት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ካሳ፤ በተቋማት ላይ ሙያን መሰረት ያላደረግ ምደባ መልሶ ችግር ላይ እንዳይጥለን መንግስት ጉዳዩን በአንክሮ ሊመለከተው ይገባልም ብለዋል።