ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ያግዛል የተባለው ዘመናዊ የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ተመረቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 ሰላም የህጻናት መንደር ያስገነባው ዘመናዊ የአሸከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ዛሬ ተመርቆ ስራ ጀመረ።

ማሰልጠኛው በአገሪቷ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እንደሚያግዝም ተገልጿል።

በፕሮግራሙ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/UNIDO የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተርና በኢትዮጵያ የጃፓንና ስዊድን አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት  እንዳሉት " በኢትዮጵያ 75 በመቶ የትራፊክ አደጋ የሚከሰተው በአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስ" ነው።

በአገሪቷ የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች ተብለው የተለዩት የአሽከርካሪዎች ባህሪና ብቃት ማነስ፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ሁኔታ እና የመንገዶች ደህንነት ናቸው ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው ምሳሌ የአሽከርካሪዎች ማስልጠኛ ማዕከል ስራ መጀመሩም በትራፊክ አደጋ የሚጠፋውን የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማሰልጠኛው የአካዳሚ ብቃትና ክህሎት እንዲሁም የተሻለ ስነ ምግባር ያላቸውን አሽከርካሪዎችን አሰልጥኖ ለማውጣት የሚያስችል እና ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ተቋም የብቃት ማረጋገጫ የተሰጠው ነው ብለዋል።

በአገሪቷ ያሉት የአሽከርካሪ ማስልጠኛ ተቋማት ብቃት ያላቸውን አሽከካሪዎች በማሰልጠን በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ መስራት አለባቸው፤ ለዚህም ሚኒስትሩ በቀጣይ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።

የሰላም ህጻናት መንደር ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጫሊ እንዳሉት ምሳሌ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም የከባድ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ሲሆን በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማሰልጠን የተቋቋመም ነው ።

ተቋሙ በዩኒዶ፣ ሲዳ፣ ቮልቮ እና ሰላም የህጻናት መንደር በጋራ የተቋቋመ መሆኑንና ፕሮግራሙ ለ5 ዓመታት እንደሚቆይ ተጠቅሷል ።

ሰላም የህጻናት መንደር ባለፉት አምስት አመታት አብዛኛውን ሴቶችን ያካተተ የከባድ ተሸከርካሪ መካኒኮችን ማሰልጠኑን ጠቅሰው አሁን የተጀመረው አሽከርካሪዎች ስልጠና በመንደሩ 11ኛ ፕሮግራም ነው ብለዋል።

አካዳሚው በሲሙሌተር/በዲጂታል መለማመጃ/ ሲሪ ዲ አማካይነት ስልጠና የሚሰጥበትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደገፈ ሲሆን በተቋሙ አነስተኛ ስልጠና ተምሮ ለማጠናቀቅ ቢያንስ 6 ወራት ይፈጃልም ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት /UNIDO/ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኦሬሊያ ካላብሮ እንዳሉት ማሰልጠኛ ተቋሙን በቴክኒካል ዘርፍ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኪ ማትሱናጋ በበኩላቸው የጃፓን  መንግስት በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ሪፎርም የተፈለገውን ለውጥ እንዲያመጣ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ማሰልጠኛ ተቋሙ የአሽከርካሪዎች ብቃት ለማሳደግ እንዲያስችለው ኩባንያው ለስልጠናው የሚያግዝ 3 ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለግሷልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም