የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሔራዊ እግር ቡድን የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ማምሻውን ከማሊ ጋር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሔራዊ እግር ቡድን የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ማምሻውን ከማሊ ጋር ያደርጋል
አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ማምሻውን ከማሊ አቻው ጋር ያደርጋል።
ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ የሚካሄደው ጨዋታው በጃፓን ቶኪዮ እ.አ.አ በ2020 ለሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ የሚደረግ የማጣሪያ ጨዋታ ነው።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረጉት ጨዋታ ለኢትዮጵያ ደስታ ደሙ፤ ለማሊ ሳማዲያሬ ዲያንካ ባስቆጠሯቸው ግቦች አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ዛሬ 35 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው በሞዲቦ ኬይታ ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ግብ አስቆጥሮ የተመለሰው የማሊ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉ ሰፊ ነው።
ብሔራዊ ቡድኑ 18 ተጫዋቾችን ጨምሮ 27 ልዑካንን በመያዝ የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ባማኮ ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ማቅናቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ ገልፀዋል።
የ37 ዓመቱ ጊኒ ቢሳዊ ጂልቤርቶ አንቶኒዮ ዶስ ሳንቶስ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የማሊ አቻውን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በቀጣዩ ዙር ከካሜሮን አቻው ጋር ይገጥማል።
ኢትዮጵያ ይህን ዙር ካለፈች ደግሞ በታህሳስ 2012 ዓ.ም በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ አገሮች የኦሎምፒክ ውድድር የመሳተፍ አድል ይደርሳታል።
በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከወጣች ደግሞ ለቶኪዮ የእግር ኳስ ውድድር በቀጥታ አልፋ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ትሳተፋለች ማለት ነው።
ጃፓንን ጨምሮ 16 አገሮች በሚሳተፉበት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከአፍሪካ አህጉር በወንዶች እግር ኳስ ሶስት አገሮች ይወከላሉ።
የኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሮች ለመሳተፍ በተለያዩ ጊዜያት የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን እ.አ.አ በ2004 በአቴንስ ፣ እ.አ.አ በ2008 በቤጂንግ አሎምፒክ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1956 በአውስትሪሊያ ሜልቦርን ኦሎምፒክ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታ ማድረጓን መረጃዎች ያመለክታሉ።