ቀጥታ፡

ከለገዳዲ ግድብ ወደ አዲስ አበባ ውሃ የሚያሰተላልፈውን መስመር ጥገና ማጠናቀቁን ባለስልጣኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 ከለገዳዲ ግድብ ወደ አዲስ አበባ ውሃ የሚያሰተላልፈው መስመር ላይ ተፈጥሮ የነበረው የብይድ መልቀቅ ጥገና መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

ከግድቡ ወደ አዲስ አበባ ከሚያስተላልፉ መስመሮች አንዱ የሆነው ባለ 900 ሚሊ ሊትር ከባድ የውሃ መስመር ረጅም ጊዜ ከማገልገሉ የተነሳ ዓርብ ምሽት ላይ የብይድ መልቀቅ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ በአያት፣ ሰሚት፣ መገናኛ፣ ኮተቤ፣ ሃያ ሁለት፣ ቦሌ አየር መንገድ፡ ቦሌ ሚካኤልና ኡራኤል አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠ ሲሆን በአራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፡ ፒያሳ፡ ጥቁር አንበሳ እና ተክለኃይማኖት አካባቢ በከፊል የውሃ አገልግሎት ተቋርጧል፡፡

የውሃ መስመሩን የመጠገን፣ የማጠብና አየር የማስተፈንስ ስራ የተሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ውሃ እየተቆራራጠ መውረድ መጀመሩን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

በመስመሩ ስብራት ምክንያት ውሃ የተቋረጠባቸው አካባቢዎችም የውሃ ግፊት በሚያደርሰው ቅደም ተከተል መሠረት የውሃ አገልግሎት እንደሚያገኙ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም