ሉሲዎቹ ለአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ወደ አልጄሪያ ያመራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሉሲዎቹ ለአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ወደ አልጄሪያ ያመራሉ
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ ጋና ለምታስተናግደው 11ኛው የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ለሚያደርጉት የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ነገ ወደ አልጄሪያ ያቀናሉ። የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ከህዳር 8 እስከ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል። ሉሲዎቹ በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ መጋቢት 2010 ዓ.ም ከሊቢያ አቻቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ በደርሶ መልስ ውጤት 15 ለ 0 ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል። በቀጣይ በጋና በሚካሄደው ውድድር ለመሳተፍ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም ከአልጄሪያ ጋር አልጀርስ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋሉ። የፊታችን ረቡዕ ለሚያደርጉት ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ወደ አልጄሪያ እንደሚያቀና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። አሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ ለአንድ ወር በአዲስ አበባ ስታዲየም 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምድ ሲያደርጉ የቆየ ሲሆን የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችንም ከአገር ውስጥ ክለቦች ጋር አድርገዋል። በጉዳት ምክንያት ከልምምድ ርቃ የነበረችው ሎዛ አበራ ከጉዳቷ አገግማ በዚህ ሳምንት ከቡድኑ ጋር መደበኛ ልምምድ ሰርታለች። የደደቢት አጥቂ የሆነችው ሎዛ አበራ በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የማጣሪያውን ኮከብ አግቢነት በመምራት ላይ ትገኛለች። ሌላኛዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጥቂ ረሂማ ዘርጋው በማጣሪያው አራት ግቦችን በማስቆጠር ሎዛን ትከተላለች። ሉሲዎቹ ከአልጂሪያ ጋር የመልሱን ጨዋታ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል። በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፉ ለአራተኛ ጊዜ በአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ መካፈል ይችላሉ ማለት ነው። ሉሲዎቹ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2002 ውድድሩ ለአምስተኛ ጊዜ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ተሳትፎ ከምድባቸው ያላለፉ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ስድስተኛው ውድድር በማሊ ተሸንፈው አራተኛ ደረጃን በመያዝ ያስመዘገቡት ውጤት በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛ ነው።