ቀጥታ፡

የአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር አባላት አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 የአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር አባላት ለዓመታዊው የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባና ለጉብኝት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።

አባላቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ ሃላፊዎችና የአስጎብኚ ድርጅቶች የስራ ሃላፊዎች አቀባባል አድርገውላቸዋል።

የማህበሩ አባላት ከመጋቢት 16 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቆይታ ይኖራቸዋል።

የአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር በስሩ ካቀፋቸው 166 የአስጎብኚ ድርጅቶች መካከል የ40ዎቹ ድርጅቶች ተወካዮች ለቦርድ ስብሰባውና ለጉብኝቱ አዲስ አበባ ተገኝተዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ቴሪ ዴል እንዳሉትም ማህበሩ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ በረጅም ጊዜ የቱሪዝም ዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ በማሳደግ የኢኮኖሚው መስክ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራ ይሰራል።

በአሁኑ ሰዓት በማህበሩ ስር የሚገኙ 166 የአስጎብኚ ድርጅቶች በየዓመቱ 19 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እያመነጩ መሆኑንና በቅርብ ጊዜም ከዚህ ገቢ ውስጥ ብዛት ያለው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

ይህ እውን እንዲሆንም መጀመሪያ በማህበሩ ስር የሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለውን የዘርፉን አቅም እንዲያውቁ ማድረግ እንደሚያስፈልግና በቀጣይ ጊዜያትም የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪስት መዳረሻነት ተፈላጊ ከሆኑ 10 አገራት ውስጥ አንዷ እንደሆነችና በየዓመቱም  48 በመቶ የቱሪዝም እድገት እያሳየች መምጣቷ ማህበሩ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎት እንዳሳደረበት አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም  ከስብሰባውና ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ከአስጎብኚ ድርጅቶችና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንዲሚያደርጉም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ በሞቱት ሰዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘንም በማህበራቸው ስም ገልጸዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ቱሪስቶች ከፍተኛ መዳረሻና የገበያ አቅም መሆን እንደምትችል ገልጸው፤ የአሜሪካ አስጎብኚ ድርጅቶች ጥያቄም በኢትዮጵያ ለዚሁ የሚሆን መሰረተ ልማትና "አድቬንቸር ቱሪዝም" በቂ መረጃ አለማግኘት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እነዚህን ጥያቄዎች ከመለሰችና አስፈላጊውን ነገር ካሟላች የአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች የአፍሪካን የገበያ ድርሻ ግማሹን ማግኘት እንደምትችል በማውሳት።

ከአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራት የሚቻልበት ሁኔታ፣ለአሜሪካ ጎብኚዎች በሚዘጋጁ የጎዞ ፓኬጆችና የአሜሪካን ሰፊ የገበያ አቅም መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

በአጠቃላይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስክ በማሳደግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማገዝ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የ "ኢትዮጵያን ሆሊደይስ" ስራ ክፍል ሃላፊ አቶ ዘውዱ ሃይለማርያም በበኩላቸው ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከአሜሪካ ውጪ የሚያደርገውን የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብስባ በኢትዮጵያ እንዲያደርግ አየር መንገዱ ለሁለት ዓመታት ያደረገው ጥረት ውጤት አግኝቶ የማህበሩ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ችለዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የአሜሪካ ዜጎችን ቁጥር  ከመጨመር አንጻርም የማህበሩ መልካም ተጽእኖ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።

የአስጎብኚ ድርጅቶቹ ወደ አሜሪካ ሲመለሱ በኢትዮጵያ ያለውን ነገር በማስተዋወቅ የቱሪዝም አምባሳደሮች ሆነው እንደሚያገለግሉም ጠቅሰዋል።

የአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር በአዲስ አበባ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሳባ የሚያደርጉ ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችንና ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በማቅናትም በባህርዳር፣ ላሊባላና ጎንደር  የቱሪስት መዳረሻዎችን እንደሚጎበኙም ተገልጿል።

የአሜሪካ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር እ.አ.አ በ1972 በካሊፎርኒያ በሚገኙ የእስጎብኚ ድርጅቶች የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫው ኒው ዮርክ ከተማ ናት።

ማህበሩ በየዓመቱ  በዓለም አቀፍ ደረጃ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጎብኚዎችን የሚያስጎበኝ ሲሆን በማህበሩ ስር ያሉ 166 የአስጎብኚ ድርጅቶች 10 ቢሊዮን ዶላር የእቃዎችና የአገልግሎቶች ግዢ እንደሚፈጽሙም መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም