ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር አምስተኛ ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 ስምንት ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር አምስተኛ ጨዋታዎች ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ይካሄዳል። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ከወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ከጠዋቱ 3 ሰአት ከ30 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሃዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እስካሁን በተካሄዱ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 13 ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማ፣ ሃዋሳ ከተማና ጎንደር ከተማ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻው ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከጎንደር ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። በኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ አራት ቡድኖች በመወዳደር ላይ ይገኛሉ። በሴቶቹ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ፣ ጎንደር ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በሁለቱም ጾታዎች የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም