የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናችን የማገዶ እንጨት መቆጠብ ችለናል....አርሶ አደሮች

82

ወልዲያ መጋቢት 14/2011 በሰሜን ወሎ ዞን የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናችን የማገዶ እንጨት መቆጠብ ችለናል፤ በጢስ ከመታፈንም ድነናል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በተያዘው ዓመት 357 የቤተሰብ ባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

በዞኑ ግዳን ወረዳ ቀበሌ 06 የሚኖሩት ወይዘሮ ታክላ ያለው ለኢዜአ እንደተናገሩት ቀደም ሲል ስድስት አባላት ያለውን ቤተሰባቸውን ምግብ በየቀኑ የሚያበስሉት በባህላዊ ምድጃ በጢስ እየታፈኑ ነበር፡፡

በሚጠቀሙት ማገዶ ከሚወጠው ጢስም በተደጋጋሚ ለዓይን በሽታ ይጋለጡ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ የባዮጋዝ ጋዝ ቴክኖሎጂን ለምግብ ማብሰያነት በመጠቀማቸው ከችግሩ መላቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡

የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በመሆናቸው ደን በመጨፍጨፍ ለማገዶ ይጠቀሙበት የነበረውን እንጨት ለማዳን እንደቻሉም ገልፀዋል፡፡

በመቄት ወረዳ ቀበሌ 28 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መልኬ ወዳጀ በበኩላቸው " የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ከምግብ ማብሰያ ባለፈ ለመብራት አገልግሎት እየተጠቀምንበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም በእንጨት ጢስ ታፍነው ሲደርስባቸው ከነበረው የጤና እክል እንደታደጋቸውም አመልክተዋል።

ከባዮጋዝ ቴክኖሎጂው የሚገኘውን ቅሬት በማዳበሪያነት በመጠቀም ለሰብል ልማት እየተጠቀሙ መሆናቸውንም ወይዘሮ መልኬ ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ የባዮጋዝ ባለሙያ አቶ መኮንን አስፋው የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሙያው እንዳሉት በዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት 380 የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂዎች ተገንብተው አርሶ አደሩን ለምግብ ማብሰልና ለመብራት አገልግሎት እንዲጠቀምባቸው ተደርጓል።

በዚህ ዓመትም ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ 357 የቤተሰብ ባዮጋዝ በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በግንባታ ላይ ካሉት መካከል የ60ዎቹ ግንባታ ተጠናቆ  አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን ቀሪዎቹ እስከበጀት ዓመት ማብቂያ ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ አመልክተዋል፡፡

በዞኑ እስካሁን የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የባዮ ጋዝ ማብላያዎች በዓመት 9 ሺህ 120 ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድ ከአየር ማስወገድ ከማስቻላቸው በላይ 164ሺህ 160 ቶን እንጨትም ከውድመት ለመጠበቅ ያግዛሉ መባሉ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም