ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ተጀመረ

137

መቀሌ መጋቢት 14/2011 ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች የልዩ ልዩ ስፖርት  ውድድር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀመረ።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ውድድሩን ሲያስጀምሩ እንዳሉት ስፖርት ለጤንነት ብቻ ሳይሆን ለአእምራዊ ብስለትና እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ወጣቶች ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ ሊተጉ ይገባል።

ከየክልሎች ትምህርት ቤቶች የተወጣጡት የስፖርት ውድድሩ ተሳታፊዎች የሰላምና የፍቅር አምባሰደሮች ሆኖው እንዲያገለግሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዚሁ ስነስርዓት ወቅት የተገኙ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድሩ ተሳታፊ ወጣቶች  የየአካባቢያቸውን ባህል ፣ ቋንቋ እና ታሪክ በመለዋወጥ የመከባበር ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ለማጠናከር እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ ለመለየት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ወጣቶች  ጥራት ያለው ትምህርት ከመቅሰም በተጨማሪ ለሰላም ፣ ለፍቅር ፣ ለአንድነትና ለእድገት እንዲሰሩም መክረዋል፡፡

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነት አቶ ላ በመድረኩ የተገኙ የስፖርት ኮምሽን ኮምሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው በትምህርት ቤቶች መካከል የሚካሄደው የስፖርት  ውድድር ሀገሪቱ  ብቃት ያላቸው ስፖርተኞች በብዛት ለማፍራት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች ከአላስፈላጊ ቦታ በመራቅ ተመራማሪ እንደሆኑ የሚያግዘውን የስፖርት እንቅስቃሴን በየአካባቢያቸው እንዲያዘወትሩ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ  ናቸው፡፡

እስከ መጋቢት 28/2011ዓ.ም. ድረስ በሚቆየው በዚሁ ሀገር አቀፍ  የትምህርት ቤቶች ውድድር ከ3ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በ20 የስፖርት ዓይነቶች በሚካሄደው ውድድር በበጀት  ችግር ምክንያት ሶማሌና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዳልተሳተፉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም