በብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሰለጠኑ 22 ሴቶች ተመረቁ

59

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሎክ ቼይን በተባለው የቴክኖሎጂ  አጠቃቀም የሰለጠኑ 22 ሴቶች ተመረቁ።

ቴከኖሎጂው የኮምፒውተር መረጃዎችን ባልተማከለ መልኩ መዝግቦ የሚይዝ፣ የማይሳሳት፣ የማይሰረዝ፣ የማይጭበረበርና በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትም የማይዘረፍ የአሰራር ሥርዓት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንኑ ቴክኖሎጂ (ብሎክቼን) ለመሬት አስተዳደር፣ ለምርጫ፣ ለኤሌክትሮኒክስ ግብይትና ለመሳሰሉት ስራዎች ጥቅም ላይ የማዋል ፍላጎት አለው ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከእንግሊዙ "IOHK" ኩባንያ ጋር በመተባበር ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ተከታትለው ከተመረቁት መካከል 18ቱ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ አራቱ ኡጋንዳዊያን ናቸው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የዲጂታል ዓለምን በመፍጥነት ለመቀላቀል ተመራቂዎቹ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል።

በቢዝነስ ዘርፍ፣ በመልካም አስተዳደርና ፍትህ ዘርፎች ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ በማበጀት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራት የእናትፋንታ ሺፈራው እንዳለችው ቴክኖሎጂው አገልግሎት ሲጀምር የተሻለ ስራ መስራትና አገሯን ማገልገል ትሻለች።

ከእንግሊዙ "IOHK" ኩባንያ ለትምህርት ተቋማት፣ ለመንግስታዊ አካላት እንዲሁም ለማህበራት በክሪፕቶከረንሲ እና በብሎክ ቼይን ስልጠና የሚሰጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተሰጥኦ ያለው የሰው ሃይል ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም