ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ስሜን እያጠፉ ያሉ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃንን በህግ እጠይቃለሁ አለ

አዲስ አበባ  መጋቢት 14/2011 በተለያዩ የውጭ የመገናኛ ብዙሃን የአየር መንገዱን ስም የሚያጠፉ ጋዜጠኞችንም ሆነ የመገናኛ ብዙሃኑን በሕግ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለፀ።

አየር መንገዱ ለአብራሪዎቹ በምስለ-በረራ የተሟላ ስልጠና በመስጠት ክፍተት አለበት ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ሳይጣራ የወጣ የሀሰት መረጃ ነው ብሏል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከሰሞኑ በኒውዮርክ ታይምስ እና ዋሽንግተን ፖስት የወጡ ዘገባዎችን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ ''በቅርቡ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪ የማክስ 8 ምስለ-በረራ (ሲሙሌተር) ስልጠና አልወሰደም'' የሚል ዘገባ ማውጣታቸው ይታወሳል።

አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰባት የምስለ-በረራ ማሰልጠኛ መሳሪያ ያለው ሲሆን አብራሪዎቹ አስቀድመው በቂ ስልጠና እንደሚወስዱና ወደ ስራ እንደሚሰማሩ ነው የጠቆሙት።

የምስለ-በረራ መሳሪያው እያንዳንዱ ከ23 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበትና ከኢትዮጵያ አልፎ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም በኒውዮርክ ታይምስና በዋሽንግተን ፖስት የወጣው ዘገባ ከእውነት የራቀና ኃላፊነትና ማስረጃ የጎደለው ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ ቦይንግ ኩባንያ ባፀደቀውና በሚያዘው የስልጠና መርሃ-ግብር መሰረት አብራሪዎቹን አሰልጥኖ እንደሚያዘጋጅ የገለጹት አቶ ተወልደ ሰሞኑን በተከሰከሰው የአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡት ሁለት አብራሪዎችም በምስለ-በረራው የታገዘ ስልጠና ወስደዋል ነው ያሉት።

የአየር መንገዱ የበረራ መምሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካፒቴን ዮሐንስ ኃይለማርያም በበኩላቸው ማንኛውም አውሮፕላን ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት መመሪያው ቀድሞ እንደሚደርስና አብራሪዎቹም እንደሚዘጋጁበት ነው የገለጹት።

የቦይንግ ኩባንያ አደጋው ከደረሰ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያ አደርጋለሁ ያለው የዘገየ ውሳኔ መሆኑንም ገልፀዋል።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓም ማለዳ የ35 አገራት ዜጎችን ይዞ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ይጓዝ የነበረ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተከስክሶ 157 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም