ቀጥታ፡

በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የአመራር ምርጫ ምክንያት የፕሪሚየር ሊጉ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንዲራዘሙ ተደረገ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከነገ በስቲያ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በሚያካሂደው የፕሬዝዳንት እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወደ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ተዘዋውረዋል። የ25ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ እንዲካሄዱ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው የነበረ ቢሆንም እሁድ በሚካሄደው ምርጫ ምክንያት ጨዋታዎቹ ወደ ማክሰኞ እንዲራዘም መደረጉን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ወልዲያ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከቀኑ 11 ሰአት ከ30 ላይ ደደቢት ከአርባ ምንጭ ከተማ ይጫወታሉ። በጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከመከላከያ የሚያደርጉት ጨዋታ ማክሰኞ ከረፋዱ አራት ሰአት ላይ የሚደረግ ይሆናል። በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና እና በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከኢትዮ ኤሌትሪክ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ። በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ በሚደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ መቐለ ከተማን ያስተናግዳል። በ25ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች መካከል በጅማ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ውጤት በፕሪሚየር ሊጉ እያደረጉት ባለው የዋንጫ ግስጋሴ ወሳኝነት ይኖረዋል። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ የሚሰለጥነውና ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ጅማ አባጅፋር በፕሪሚየር ሊጉ እያሳየ ያለው ግስጋሴ አስገራሚ የሚባል ነው። በአንጻሩ በፖርቹጋላዊው ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮው በሊጉ ያለው አጀማመር ደካማ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ያሳየው የአቋም መሻሻልና ያስመዘገበው ውጤት ወደ ፕርሚየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር እንዲመለስ አስችሎታል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በመሸጋሸጉ ምክንያት እስከ መጨረሻው (30ኛ ሳምንት) ያሉ ሁሉም መርሃ ግብሮች ላይ የቀን ማስተካከያ ተደርጓል። በማስተካከያው ምክንያት ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ይጠናቀቅ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሁን ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ከተማ በ42 ነጥብ ሲመራ፣ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 41 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊው ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ15 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በ11 የኢትዮ ኤሌትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በ10 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም