ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬና ነገም ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬና ነገም ይቀጥላሉ።

ትናንት በተደረገው ጨዋታ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ በመታገዝ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል።

ውድድሩ ዛሬ ቀጥሎ ሲውል በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት መከላከያ የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል።

በሀዋሳ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ።

በነገው ዕለትም በፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በክልል ከተሞች በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ፣ በሀዋሳ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ከፋሲል ከተማና በሽሬ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ሲዳማ ቡና ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ38 ነጥብ ሲመራ፣ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ ፋሲል ከተማ በ28 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በተመሳሳይ 11 ግቦች ሲመሩ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ10 ግቦች ይከተላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም