የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ስምምነት አፍሪካውያን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ነው-- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ስምምነት አፍሪካውያን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ነው-- ምሁራን
አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችው የሰላም ስምምነት ለአገሪቱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ከመሆኑም በላይ አፍሪካውያን ያላቸውን ግጭቾች በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ምሁራን ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት "አዲስ ወግ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ዛሬ ተጀምሯል።
''የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የአፍሪካ ተሳትፎ'' በሚል መሪ ሐሳብ ላይ የተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ዋና ረዳት ፀሐፊ ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ፣ የአፍሪካ ህብረት አማካሪ አቶ አብዱል ሙሐመድ፣ የቀድሞ ዲፕሎማት እና የተባበሩት መንግስታት አማካሪ አምባሳደር ኀሩይ አማኑኤል እና የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ሰለሞን አየለ በመድረኩ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለምትከተለው ፖሊሲ ተሳታፊዎቹ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
በአፍሪካ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም እስራኤል ተፅዕኖ ፈጣሪ አገሮች በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ጋር ስለሚኖራት ግንኙነት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው እንዴት እንደታየ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጥያቄ አቅርበዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤደን ጋሻው የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን ከእስራትየተፈቱ ሲሆን በኤርትራ መንግስት ታስረው የነበሩ ግን ለምን እንዳልተፈቱ ጠይቀዋል።
እንዲሁም ከኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የኤርትራ ዜጎች በአዲስ አበባ መኖር በመጀመራቸው በከተማዋ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር መንስዔ በመሆኑ እርቀ ሰላሙ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስገኘው ጠቀሜታ ምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
አቶ ኃይሌ የተባሉ ኤርትራዊ በሰጡት አስተያየት በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው ግንኙነት ተቋማዊ ማድረግ ሲገባ ግለሰባዊ መሆን የለበትም፤ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የኤርትራ ህዝብ ያገለለ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጌታሁን ካሳ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት አልጋ በአልጋ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ በግንኙነቱ ላይ መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች አስተካክሎ መቀጠል ላይ በመንግስት የተያዘውን አቅጣጫ ጠይቀዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በቆየችባቸው ሁለት ዓመታት ድምጸ ተአቅቦ በማድረጓ እንዴት እንደ ድል ይቆጠራል ሲሉ ጠይቀዋል።
አቶ ዮሐንስ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከውስጥ የሚመነጭ አጀንዳዋ ምን እንደሆነ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ዘንድ የምትከተለው ፖሊሲ ምንድን ነው? በኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት የህብረቱ ሚና ምን እንደነበረ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ሰለሞን አየለ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት አገሪቱ ካስመዘገበችው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ባሻገር አፍሪካውያን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ነው።
''የሁለቱ አገሮች የሰላም ስምምነት ፊርማ በሳዑዲ አረቢያ ከሚደረግ ይልቅ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ቢደረግ ኖሮ ያማረና ዓለምን የሚያስደምም ይሆን ነበር'' ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በቆየችባቸው ጊዜያት በምክር ቤቱ በሚካሄዱ ውይይቶች የአገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ስትሳተፍ እንደነበረም ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል።
በተለይ ምክር ቤቱ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሰላም ዙሪያ ውይይት ባደረገበት ወቅት ኢትዮጵያ የነበራት ሚና ትልቅ አገር መሆኗን ለማሳየት ዕድል የፈጠረ እንደነበረም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ በሚካሄዱ ውይይቶች ላይ የነበራት ተሳትፎ በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ እንደነበረም ዶክተር ሰለሞን አስረድተዋል።
የአፍሪካ ህብረት አማካሪ አቶ አብዱል ሙሐመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ላይ ያላት ሚና በተመለከተ ከህብረቱ ምስረታ ጀምሮ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ ሚና ነበራት ብለዋል።
ህብረቱ በአምስት ቀጣና የተዋቀረ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱል በቀጣናው ግዙፍ ከሚባሉት አገሮች ውስጥ በምዕራብ ናይጄሪያ፣ በደቡብ ደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን ግብዕና አልጄሪያ ሲሆኑ በምስራቅ ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን አመልክተዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በአካባቢው ያለውን ሰላም ከመጠበቅ አኳያ 47 በመቶ የሚሆነው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአፍሪካ አገሮች ሲሆን የአንበሳውን ድርሻ ኢትዮጵያ መያዟን አቶ አብዱል አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ዋና ረዳት ፀሐፊ ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ እንዳሉት ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል።
በቀጣናው ያለው የመልከዓ ምድራዊ ፖለቲካ በመተማመን ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ የገለጹት ወይዘሮ ሂሩት ኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት አማካሪ አምባሳደር ኀሩይ አማኑኤል በበኩላቸው በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ጥሩ ግንኙነት ቢኖርም እስራኤል በምታደርገው ድጋፍ በአካባቢዋ ላሉ አገሮች ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአካባቢው አገሮች ዘንድ ሰላም ለማስፈን የምታደርገው ጥረት በተባበሩት መንግስታት ዘንድ ያላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትየተዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ነገ ቀጥሎ የሚውል ሲሆን ''የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ሥራ ፈጠራና ማህበራዊ አካታችነት'' በሚል ርዕስ ጠዋት የሚካሄድ የውይይት መርሐ ግብር ነው።
ከሰዓት በኋላ በሚኖረው መርሐ ግብር ደግሞ ''የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ማጽናት በኢትዮጵያ፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አካሄዶች'' ላይ ውይይት ይካሄዳል።