የህክምና ስህተቶችን ለመፍታት የሚያግዝ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የህክምና ስህተቶችን ለመፍታት የሚያግዝ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሆነ
አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትና የህክምና ስህተትን ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ ፕሮጀክት ተግባር ላይ ማዋሉን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ጤና ተቋማት ውስጥ ከህክምና ስህተት ጋር በተያያዘ የህይወት መጥፋትና አካላዊ የጤና ጉዳቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል።
የመስኩ ተማሪዎች በሙያ ስነ ምግባር ላይ ያላቸዉ የእዉቀት ክፍተት የህክምና ስህተት እንዲፈጠር ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ይነገራል።
ፕሮጀክቱ ሀኪሞች ሙያው ስነ-ምግባርና ህጎች የጎለበተ እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ተግባራቸውን በጥራት የሚወጡበትን አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ የህክምና ማህበር የተዘጋጀው ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከህግ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ሲሆን በጤና ሚኒስትር የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል።
በቅድሚያ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ እና በትግራይ ክልል ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ሥራ ላይ ይውላል ተብሏል።
የማህበሩ ሰብሳቢ ዶክተር አዳሙ አድሴ ፕሮጅክቱ በህክምና የሙያ ስነ-ምግባር የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የሙያ ስነ ምግባርና የሙያ ህጎችን በማስተማር በእዉቀትና በክህሎት እንዲሰሩ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
በተጨማሪ ህግ አዉጪ እና አስፈፃሚ አካላትም በህክምና ህግና የሙያ ስነ ምግባር የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት እንደሚያስችላቸውም ዶክተር አዳሙ አክለዋል።
በጤና ሚኒስትር የጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ቤዛ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ባለሙያዎች ስራ ከመጀመራቸዉ በፊትና ከጀመሩ በኋላ የህክምናን የሙያ ስነ ምግባር እዉቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ከህግ አንጻር ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮችን ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን ግንዛቤ በመፍጠር፤ በህክምና ስህተት የተፈጠሩ ችግሮችን ከህግ አንፃር እንዴት መታየት እንዳለባቸዉ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።
የህክምና ስህተት የሚፈጠረው በስነ ምግባር ችግር ብቻ ሳይሆን በመድኃኒት አቅርቦትና በመሳሪያዎች ችግርም ጭምር መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ባለሙያዎች የህግ ከለላ እንዲደረግላቸዉም ከማህበሩ ጋር በመተባበር እየሰራን ነዉ ብለዋል።
የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት የህክምና ስነ ምግባርን በተመለከተ የተዘጋጀ "የማስተማሪያ መፅሃፍ" ባለመኖሩ ተማሪዎች በሙያ ስነ ምግባር ላይ ያላቸዉ የእዉቀት ክፍተት የህክምና ስህተት እንዲፈጠር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
ይህንን ችግር እንደሚቀርፍ የታመነበት ፕሮጀክት ለአንድ አመት አገልግሎት እንዲሰጥና ዉጤቱን መሰረት በማድረግና በረጅም ጊዜ እቅድ ዉስጥ በማስገባት የሚታዩትን ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።