በትግራይና አማራ ክልሎች የመቀንጨርና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ስምምነት ተፈረመ

76

መቀሌ መጋቢት 13/2011 በትግራይና በአማራ ክልሎች  በህፃናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨርና ተላላፊ  በሽታዎችን ለመከላከል የሶስትዮሽ  ስምምነት ዛሬ ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የሁለቱም ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና የትምህርት ሚኒስቴር ናቸው፡፡

በትግራይ በኩል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር  ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ ፣ ከአማራ ክልል የትምህርት ቢሮው ምክትል ኃላፊ   አቶ ሙላው አበበ እና ትምህርት ሚኒስቴር በመወከል የፈረሙት ደግሞ  ዶክተር  ሲሳይ ሲናሞ በሚኒስትሩ የፌደራል ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ከፍተኛ የፕሮግራም ስራ አስኪያጅ  ናቸው።

ዓላማውም በሁለቱም ክልሎች በንፅህናና በአመጋገብ ጉድለት ለመቀንጨርና ለተላላፊ በሽታዎች የሚጋለጡ እድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለመጠበቅ  በተማሪዎች በኩል በማስተማር እያንዳንዱ ቤት እንዲደርስ ለማድረግ  መሆኑ ተገልጿል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ጉድለቶችን ለማስወገድ የሚያስችል ትምህርት በየትምህርት ቤቱ በመስጠት እናቶችን ጨምሮ ቤተሰቡ ሙሉ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ይስራል፡፡

ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ እንዳሉት  ሁለቱ ክልሎች በሚያዋስኗቸው የተከዜ ተፋሰስ የሚገኙ 33 ወረዳዎች ተግባራዊ ይሆናል፡፡

በወረዳዎቹ  ከሚገኙ 218ሺህ ህፃናት ውስጥ 50 በመቶ  በአመጋገብ ጉድለት ለመቀንጨር እና በንጽህና ጉድለት ደግሞ 21 በመቶ ለተላላፊ በሽታዎች እንደሚጋለጡ አስረድተዋል፡፡

"በህጻናት  ላይ ለሚያጋጥመው የመቀንጨርና ተላላፊ  በሽታ ለመከላከል በ287 ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች አደጋውን እንዲያውቁ የማስተማር ስራ ይካሄዳል "ብለዋል፡፡

በየትምህርት ቤቱ የሚማሩ ህፃናትም በየቤታቸው እየሄዱ ከ1ሚሊዮን ለሚበልጡ ቤተሰቦቻቸው እንዲያስተምሩ ክትትል እንደሚደረግ ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

"ትምህርት ሚኒስትር በተከዜ ተፋሰስ ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ያለውን የመቀንጨር አደጋ ለመከላከል የሚያግዝ አልሚ ምግብ እና ሌሎች እገዛዎች ያደርጋል "ብለዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ተፈራራሚዎች   ችግሩን ለመፍታት የተቀናጀ  ጥራት እንደሚያደርጉ በየበኩላቸው ገልጸዋል፡፡

ናላ ፋውንደሽን የተባለው ድርጅት ተወካይ ሚስተር ሚኪኤለ ቢሪክ በየትምህርት ቤቱ ለሚካሄደው ለዚሁ  ፕሮግራም መሳካት በየዓመቱ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ጤናው ያልተጠበቀ ዜጋ በትምህርት ጠንካራ ማድረግ እንደማይቻል በመገንዘብ አመራሮችና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከተያዘው ዓመት ጀምሮ  እስከ 2022 ዓ.ም. እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም