ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ዘርፍ የሚመራበት ፖሊሲ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የኢትዮጵያ ስፔስ ዘርፍ የሚመራበት ፖሊሲ ዝግጀት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በፖሊሲውና በስፔስ ጉዳዮች ቁጥጥር ስርዓት ረቂቅ መመሪያ ላይ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል። 

በመድረኩ እንደተገለጸውም ፤ የበለጸጉት አገራት በዘርፉ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፣ ኢንዱስትሪውን ለማዘመንና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ሰፊ ሀብት መፍጠር ችለዋል። 

በተለይም ኢኮኖሚው ላይ እስከ 400 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ሀብት መፍጠር እንደተቻለም ነው የተገለጸው።  

በኢንስቲትዩቱ የስፔስ ፖሊሲ ፣ ስትራቴጂክ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወለል እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የስፔስ ዘርፉ ያለበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው።      

ለዚህም ምክንያቱ የአገሪቷ የሳይንስ መሰረት ዝቅተኛ መሆን፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ ደካማ የስፔስ ቴክኖሎጂ አቅም መኖር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለው ትስስር ዝቅተኛ መሆን ተጠቅሰዋል።      

መሰል ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ ውይይትና ዝግጅት የተካሄደበት የስፔስ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል ብለዋል። 

''ፖሊሲው አገራት በስፔስ ዘርፍ  የተጠቀሙባቸውን ልምዶች ቀምሮ የያዘ ነው'' ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የቴክኖሎጂ አማራጮችን የያዘና ኢትዮጵያ እንዴት መጠቀም እንዳለባት አቅጣጫዎችን አሟልቶ ያስቀመጠ ነው ብለዋል።  

ፖሊሲው የአገር ደህንነትና ሉዓአላዊነትን ለመጠበቅና ልማቱን ለማቀላጠፍ እገዛ ከማድረጉም በላይ ተቋማት እንዴት ተቀናጅተው መስራት እንደሚችሉ የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል። 

አገሪቷ በአሁኑ ወቅት የምትከተለው የእድገት መርሃ ግብሮች ከስፔስ ዘርፉ ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ፖሊሲው በዚህም ላይ አቅጣጫዎችን የያዘ እንደሆነ አብራርተዋል።    

በተለይ በኢትዮጵያ የስፔስ ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ እንዳያድግ ትልቅ ማነቆ የሆነው የሰው ኃይል እጥረት መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የሰው ኃይል በብዛት ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጎ  እንደሚሰራም ተናግረዋል። 

ፖሊስው በመስኩ የስራ ዕድል እንዲፈጠር ከማድረግ ባሻገር አገሪቷ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ሲሉም ገልጸዋል።

''በኢትዮጵያ ፖሊሲው ባለመኖሩ የቴክኖሊጂ ሽግግር ሳይፈጠር ቀርቷል'' ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ከስፔስ የሚገኘውን ግልጋሎቶች አሳጥቶናል ሲሉም ተደምጠዋል። 

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ፖሊሰውን ለመተግበርም ፍኖተ ካርታ እየተዘጀ ነው።   

በኢንስቲትዩቱ የስፔስ ጉዳዮች ቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄዋን ፀጋዬ በበኩላቸው የስፔስ ቁሶችና ተግባራት ለሰላማዊ ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ የሚያስችል የስፔስ ጉዳዮች ቁጥጥር ረቂቅ መመርያም እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።  

መመሪያው የስፔስ ቁሶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ መመዝገብና ማሳወቅ ከማስቻሉም በላይ በመስኩ የሚሳተፉ አካላት ፍቃድ አሰጣጥ ስርዓት ምን እንደሚመስልና የብቃት ማረጋገጫ ሂደቶችን ያካተተ እንደሆነም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም