የተከሰከሰው አይሮፕላን ሰለባዎች የመታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል- የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የተከሰከሰው አይሮፕላን ሰለባዎች የመታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል- የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የነበረው የቦይንግ 737 አውሮፕላን በተከሰከሰበት ቦታ ህይወታቸው ላለፈው የመታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል ሲሉ የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች የጸሎት ስነ ስርዓት ወይም ስርዓተ ቁርባን ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ለሟቾች ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል።
የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አይሮፕላን መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በደረሰበት የመከስከስ አደጋ የ 149 ተሳፋሪዎችና የ8 የበረራ ሰራተኞች በድምሩ የ 157 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።
የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሐዘናቸውን በተለያየ ሁኔታ ሲገለጹ የቆዩ ሲሆን ቦታው ብዙ ሰዎች የሞቱበት ታሪካዊ ቦታ በመሆኑም የመታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪ አቶ መንገሻ ግርማ “በጣም ያሳዝነናል አረጋገፋቸው አወዳደቃቸው ጸጸቱ ከውስጣችን አይወጣም ፤ አሁንም ይሄ መስመር በደንብ ተሰምሮ መስመሩ በደንብ ተሰርቶ እዚህ ቦታ ላይ ሐውልት ተሰርቶ ቦታው ተከብሮ በየዓመቱ እንድናስተውሳቸው እንጠይቃለን።” ብለዋል፡፡
ሌላው ነዋሪ አቶ ግርማ ጫላ በበኩላቸው “እኛ አሁን የምንለው እዚህ ለሞቱት ወገኖቻችን የሆነ ማስታወሻ ሐውልት ነገር በስማቸው እንዲቆምላቸው ነው፤ በዚህም እዚህ የወደቁትን ሰዎች ለማስታወስ እንፈልጋለን። መንግስትም ይሄን ነገር ቢያይልን ሲሉ ጠይቀዋል"
አደጋው በደረሰበት ቦታ የተገኙት የግል አውሮፕላን አብራሪ የሆኑት ካፒቴን ዮናታን መንክር በበኩላቸው አደጋው የአቪየሽን ኢንዱስትሪን ሁኔታ የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረገው ነገር የሰብዓዊነት ማሳያና የአንድነታችን መሰረት በመሆኑም የሰብዓዊነት ሐውልት በቦታው መቆም ይገባል ብለዋል።
ካፒቴን ዮናታን መንክር ይሄ ቦታ ታሪካዊ ነው፤ ስለዚህ እዚህ ቦታ ላይ መንገድ አይደለም ሐውልት አይደለም፤ብዙ ነገር መሰራት ያለበት ፤ መንግስት በዚህ ነገር ሊሰራ ይገባል። የአካባቢው ማህበረሰብ ያሳየው ነገር የሰብዓዊነት ምልክት ሊቀመጥ ይገባል። ለእኛ የአንድነታችን ምልክት ነውና ብለዋል፡፡