ለተለያዩ ምግቦች ደረጃ አለመውጣት ቁጥጥሩን አስቸጋሪ አድርጎታል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ለተለያዩ ምግቦች ደረጃ አለመውጣት ቁጥጥሩን አስቸጋሪ አድርጎታል ተባለ
አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 በኢትዮጵያ በተለያዩ ምግቦች ላይ ደረጃዎች አለመውጣታቸውን ተከትሎ በምግቦቹ ላይ ቁጥጥር ማድረግን አስቸጋሪ እንዳደረገው የኢትዮጵያ የምግብ የመድሀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በአገሪቱ በርካታ ምግቦች ደረጃ ሳይወጣላቸው ገበያ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቀሱት የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አብርሃም፤ ምግቦቹ ደረጃ ያልወጣላቸው በመሆኑ ለመቆጣጠርና እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
ደረጃዎች በለስልጣን ለምግቦቹ ደረጃ እንዲሰጥ ቢጠየቅም እስካሁን ደረጃ ያልተሰጣቸው ምግቦች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሳምሶን የሀገር ውስጥ ምግቦችን በአለም አቀፍ ስታንዳርድ/ደረጃ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ ከእውቀት ማነስም ሆነ በቂ መረጃ ባለመኖር ምግቡን ሲያመጣጥንና ሲጠነቀቅ አይስተዋልም የሚሉት ደግሞ የስነ- ምግብና የህክምና ባለሙያ ዶክተር ዘላለም ደበበ ናቸው፡፡
የምግብ ደረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይመጣጠኑ የሚዘጋጁና በየመንገዱ የሚሸጡ ምግቦች ህብረተሰቡን ስኳርን ጨምሮ ለሌሎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየዳረጉ እንደሆነም ነው ያብራሩት።
ህብረተሰቡ ለአመጋገቡ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲሁም ደረጃቸው የተረጋገጠ ምግብ በመመገብ ችግሩን ማቃለል እንደሚገባም ሙያዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ ኤጀንሲው ደረጃ ያልወጣላቸውን የምግብ አይነቶችን እየለየ ደረጃ እየሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ።
የበርበሬ፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ጠጅና የአረቄ ደረጃ ከባለፈው አመት ጀምሮ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻም ደረጃ እንደሚወጣላቸው ነው የተናገሩት፡፡
ደረጃ እየወጣላቸው ያሉ ምግቦች ቢኖሩም ደረጃ የሚወጣው በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ታይቶና በምርምርና ጥናት ተፈትሾ በመሆኑ ረጅም ግዜ እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።
አንድ ደረጃ ለማዘጋጀት በትንሹ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ይፈጃል ያሉት አቶ ይስማ እስካሁን ምግብን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰባ ደረጃዎች በኤጄንሲው ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ኤጄንሲው ጥያቄ ስቀርብለት ደረጃዎችን እያወጣ ቢሆንም አብዛኛውን ግዜ በርካታ ደረጃዎች በተቋማትም ሆነ በሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደማይተገበሩም ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ለምግብ ደረጃ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ የወጡ ደረጃዎች በአግባቡ እንዳይተገበሩ እንቅፋት ሆኗል ያሉት አቶ ይስማ፤ ደረጃ የሚወጣው ለህብረተሰቡ ጤናና ደህንነት በመሆኑ ህብረተሰቡም ሆነ ተቆጣጣሪ አካላት ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተው ሰባት አይነት ደረጃዎች ያሉ ሲሆን መጠጦችን ጨምሮ ሌሎች ምግቦች በምግብ ደረጃዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡