ዩኒቨርስቲዎች ነባር ባህሎችን ለማሳደግ በጥናትና ምርምር መደገፍ እንዳለባቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርስቲዎች ነባር ባህሎችን ለማሳደግ በጥናትና ምርምር መደገፍ እንዳለባቸው ተመለከተ
ደብረ በርሃን ግንቦት 23/2010 ዩኒቨርስቲዎች ነባር የህረተሰብ ባህሎች ሳይበረዙ ተጠብቀው እንዲያድጉ በጥናትና ምርምር መደገፍ እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡ " ባህል ለስራ ፈጠራና እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ አምስተኛው ሀገር አቀፍ የባህል አውደ ጥናት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል፡፡ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው አውደ ጥናቱ ሲጀመር እንዳሉት ጥንታዊ ባህሎች ፣ስነ-ጹህፎች፣ዕደ-ጠበባትና ወጎች ጨምሮ ሌሎችንም ይዘታቸውን ሳይለቁ ለትውልድ ማሸጋገር ይገባል፡፡ ለዚህም ዩኒቨርስቲዎች በጥናትና ምርምር በመደገፍ እንዲያድጉ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። "ትውልዱ የጥንት ማንነቱን፤ የአኗኗር ዘይቤውንና የስነ-ቃል ሀብቶችን ጠበቆ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማስፋት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ፎረም ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል "ብለዋል። ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበርም በባህርዳር ከተማ 27 ትምህርት ቤቶች ላይ የቋንቋና ባህል ማዕከል ተከፍቶ ባህሎችን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከምዕራቡ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ የአነጋገርና ቋንቋ አጠቃቀም በመላቀቅ የሀገሪቱን ባህል፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ህይወት መገለጫና ማንነት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ምሁራንም የሚሰሯቸውን የባህል ጥናትና ምርምሮችን በራሱ ብቻ ሳይሆን የአተገባበር ዘዴውንም በማሳየት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል። የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው "ያሉንን ባህል፣ ግዕዝ፣ ፊደል፣ ስነ-ስዕል፣ ስነ-ጹህፍና ስነ-ቃሎችን በጥናትና ምርምር አግዘን ጥንት ያሳየነውን የስልጣኔ ማማ ለመድገም ርብርብ ያስፈልገናል" ብለዋል፡፡ የተማሪዎችን እውቀት፣ ክህሎትና ፈጠራ ከባህል ጋር በማስተሳሰር ወደ ተግባር ለመቀየርም ከ29 በላይ ጥናቶችን በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። " ወጣት አዳዲስ ደራሲያንም ቆየት ያሉ የባህል ደራሲያን ተግባር በመዳሰስ ባህሉን ሳይለቁ እሴቶቻችን ጠብቀው ማቆየት አለባቸው" ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማረኛ ቋንቋ፣ ስነ-ጽሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው " ሀገሬ ሀገሬ" ግጥሞች በድህረ 1980ዎቹ ሴት ገጣሚዎች ምናብ የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ አቅረበዋል፡፡ ጥንት በተለያዩ ግጥሞች፤ፉከራና ሽለላዎች ማህበረሰቡን ለልማት ስራ፣ ለሀገራዊ ስሜትና ለፍቅር ደራሲያን ያነሳሷቸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ የሰውን ስሜት ብቻ ሳይሆን እንሰሳትንም በግጥም ታግዘው ዓላማቸውን ያሳኩ ነበር። የትላንቱን ባህል፣ ወግና ታሪክ በመዘከር ዛሬን ለመኖርና ነገን ለማሰብ ትውልዱ ሊማር እንደሚገባ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ያመላከቱት ደግሞ በአዲስ አበባ ኮተቤ ዩንቨርሲቲ በቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር የሻው ተሰማ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ግጥማዊ ስራዎችን በተገቢው በማስተማር ተማሪዎች ራሳቸውን አንጸው በሚሰማሩበት አካባቢ ህብረተሰቡን ማስተማር እንዲችሉ የማድረግ ኃላፊነታቸውንም ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ " ቱሪዝምን ከኢንዱስትሪው ጋር በማቆራኘት ቱባ ባህሎቻችንን ከአለም ጋር አዋህዶ ማሳየትም ይኖርብናል" ብለዋል። ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው አምስተኛው የባህል አውደ ጥናት ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ጥናታዊ ጽሁፎቹ ታትመው ለአንባብያን እንደሚደርሱም ተመልክቷል። በአውደ ጥናቱ በሀገሪቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ350 በላይ ምሁራን ተሳትፈዋል።