ቀጥታ፡

ሰብዓዊነት- በ’ዝናብ አምባ’ ግርጌ

አየለ ያረጋል-ኢዜአ.

ጋራ ቦካን ‘ዝናብ አምባ’ አልኩት። በኦሮምኛ ‘የዝናብ ተራራ’ ወይም አምባ እንደማለት ነው ይላሉ የስፍራው ነዋሪዎች። ከዛ ቅርብ ርቀት ‘ቱሉ ፈራ’ (መዘዘኛው ተራራ) ጉብታ ይታያል። በጣም ነፋሳማ ቦታ ነው። ከአምባው በስተምዕራብ ከተንጣለለው ጤፍ ማሳ ግርጌ አዳፋ ድንኳኖች ተተክለዋል። የሰርግ አጋፋሪ መሳይ ሰዎች ወዲያ ወዲህ በድንኳኑ ዘሪያ ገባውን ይራወጣሉ። ቀረብ ብሎ ያልተመለከተ የደስታ በዓል እንደሆነ ቢገመት አይፈረድበትም። ደንኳኑ ጋር ቀረበኩ። ባውንድ(ጥቁር ሻሽ) የጠመጠሙት እናት (ወይዘሮ አዛለች ከልሌ) ፊታቸውን በመዳፋቸው ከልለው ቅጭም ብለዋል። ገና ሲያዩኝ ነው ከጎናቸው ስበው ያስቀመጡኝ። ስሜታቸወን ያጋሩኝ።

ከድንኳኑ ውጭ የአበባ ጉንጉን ክምር ይታያል። በዙሪያው ደግሞ በልብሰ ተክህኖ የተዋቡ፣ መቋሚያ ጨብጠው የሚያዜሙ፣ በጽና ጭስ አካባቢውን እያጠኑ የሚታዩ ካህናት አሉ። በካህናቱ ዙሪያ የጦር ማሳሪያ የያዙ በርካታ ታጣቂዎች ሰልፍ ሰርተው ቁመዋል። ዙሪያ ገባውን ደግሞ የካህናቱን እያስተዋሉ የሚያነቡ እናቶች ይታያሉ።የነጠላቸውን ጠላት ዘቅዝቀው በሃዘን ድባብ የሚስተዋሉ እናቶች። ዙሪያ ገባወን የሰው ጎርፍ በጤፉ ማሳ ላይ ከቦ ቆማል። ተማሪዎች ትምህርታቸውን ትተው ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በዚህ ስፍራ ከትመዋል። በድንኳኖች ውስጥ በግዙፍ የጎማ በርሚሎች ጠላ ተሹሟል። ጀሪካኖችን የተጫኑ አጋሰሶች ወደ ስፍራው ይተማሉ። በትላልቅ ጎላ(ድስቶች)ሻይ እየተፈላ ነው። ይህ ሁሉ ከአንድ ወረዳ አድባራት የተውጣጣ ነዋሪ ሁሉ የተሰበሰበው ሀዘኑን ለመግለጽ ነው።

መጋቢት 12 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተከሰከሰ 12ኛ ቀኑ ነው። በሌላ አነጋገር ተከስክሶ ሕይወታቸው ያለፉ 157 ሰዎች 12ኛ ቀናቸው ነው። አደጋው የደረሰበት ስፍራ (ጊምቢቹ ወረዳ) ነዋሪዎች በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ናቸው። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት እምነትና ትውፊት ሰው በሞተ በ12ኛው ቀን ስርዓተ ቁርባን(የጸሎትና ፍታት ስነ ስርዓት) ይደረጋል። ለለቀስተኛው የሚሆን እህል፣ ውሃም(ጠበለ ጻደቅ) ይቀርባል። ጠበለ ጠዲቅ ሳይቀምሱ ከኃዘን ቦታ(ከቁርባን) መለየት በባህሉ ያስነውራል። እናም ጊምቢቹዎች ዛሬ ማንነታቸውን ለማያውቋቸው ግን በቀያቸው በአሰቃቂ የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቁርባን እያወጡ ነው። ወይዘሮ አዛላችና በስፍራው ውስጣቸው በሐዘን ተነክቶ የሚላቀሱ እናቶች ውሰጣዊ ስሜትን ይፈታተናል። ‘ረግፈው ቀሩ እንጂ’ እያሉ እንባ የሚያቀሩት ወይዘሮ አዛላች ቆሎ ቆልተው፣ ማንቆርቆሪያ ጠላ ይዘው ቁርባናቸውን ሊያወጡ ነው የተገኙት። የማህበረሰቡ አድራጎት በር?ጥም ኢትዮያዊያን ለሰው ልጆች ያላቸውን ርህራሄና የአዛኝነት ማህበራዊ እሴት ያስተምራል።

እናም የጊምቢቹ አርሶ አደሮች ዛሬ ኀዘናቸው ነው። አደጋው በደረሰ ወቅት ፈጥነው ደርሰው በወረዳው ፖሊስ የተመራ ሚሊሻም በቦታው ውሻም ሆነ አሞራ ተጎጂዎችን እንዳይነካ ተከላክለዋል። እየተላቀስን አስከሬኑ ላይ ምንም ነገር እንዳይደርስ ሲጠብቁ ሰንብተዋል። ከ33 አገራት የተሰባሰቡ ዜጎች በ ስድስት ደቂቃዎች አብረው ቢቆዩም ያጋጠማቸው ሞት አሳዝኗቸዋል። በወረዳው የሐማ ቁንጡሹሌ ነዋሪ አቶ ባቲሪ ለማ አበበ “እንደ ሰው ሰው ነን። በቀበሌያችን ያልታሰበ አደጋ ደርሶ ሰዎቹ ስጋቸውና ደማቸው ለነፋስ ነው የተሰጠው” ይላሉ። “በኛ ቀበሌ በመከስከሱ አደጋው እነሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በኛም ላይ የደረሰ አደጋ ነው። እንደ ሰው በሰውነታችን ነው የምናምነው፤ ከየትም አገር ይሁን የሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች ላይ የኀዘን ጥላሸት ፈጥሯል። ይህን ለመካፈል ነው ” ሲሉ የቁርባን መርሃ ግብሩን ለማድረግ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ደቻሳ ጉተማ “የውጭም ሆነ የውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉም የአግዚአብሄር ፍጡር ነው። ተፈጥሯችን ውስጣችን አንድ ነው፤ የኛ አስተሳስብ ይሄ በነው። ከዚህ ቦታ እንዳልሆነ መሆናቸው በጣም ተሰምቶናል። ከዛን ቀን ጀምሮ 12 ቀናችን ነው ዛሬ፤ ለቀሶው መቸም ከባድ ነው። አይተን የማናውቀው በጆሯችንም ሰምተን የማናውቀም ነው እዚጋ የወረደብን” ይላሉ። ከዛን ቀን ጀምሮ ሀዘን ላይ መቆየተያቸውን የሚናገሩት አቶ ደቻሳ “በባህላችን መሰረት ማንም ሲሞት ለሞቱት ቁርባንና ፍታት ይደረጋል፣ ዳዊት ይደገማል” የሚሉት አቶ ደቻሳ ጉተማ በደንብና ወግ መሰረት ቁርባን ማስቆረብ ወደዋል።

በስፍራው ያነጋገርኳቸው ሌላ ካህን “ቁርባን መታሰቢያ ነው። ከሰባት ጀምሮ በ12 ቀን፣ በወር፣ በ40 ቀን፣ በ80 ቀን፣ በመንፈቅና በዓመት ይደረጋል” ይላሉ። “ስጋቸው ተቆራርሶ፣ አጥንታቸው ተቃጥሎ፣ ደማቸው ፈሶ፣ አጥንታቸው ነዶ በዚህ ስፍራ በማረፋቸው በጣምን ነው እንደ ኢትዮያም አንደ ኦርቶዶክሰም፣ እንደ ካህናት ሁሉ የተሰማን” ብለዋል። ለዚህ እንደ አገራችን እንደ ኦርቶዶክስ ፍታት ልንፈታ ግንዘቱም፣ ፍታቱም እየተደገመ ነበር ያሉኝ።

ወይዘሮ ዘነበች ሽፈራው በአገልግል ቋጥረው ከአደጋው ስፍራ ደርሰዋል። "ለሞቱት ሰዎች ጠበለ ጸዲቅ ለቁርባን የሚሆን 12ታቸው ስለሆነ ሙልሙል ይዘን መጥተናል። በእራሴ ፍላጎት በራሴ አስቤ ያመጣሁት። በጣም ያሳዝናል እንደ ወጡ ያሰቡበት ባለመድረሳቸው እንደ ወጡ መቅረታቸው በጣም ያሳዝናል” በማለት በጥቁር ሻርፓቸው አይናቸውን እየጠረጉ የተናገሩት። ለዚህም የወደቁ ወገኖቻችን ለማስታወስ እርሳቸውና ሌሎች እናቶች ለቁርባን እህል ውሃ ይዘው መምጣታቸውን ነው የሚገልጹት።

የጊምቢቹዎችን ስሜት ማየት የገጠሩ ኢትዮያዊያንን የሰብዓዊነት ጥግ ይረዳል። በኀዘን ጊዜ የሰውን መረዳዳትና አብሮነት ያደንቃል። በዘርና በብሔር ለሚናቆሩ ኢትዮጵያዊያን ሀፍረት ያከናንባል። ለዚህ ምስክር አቶ ባትሪ ለማን ንግግር ማውሳት ይገባል። “ኢትዮጵያ ስትቀር ከ32 አገራት ሰብስቦ ከዚህ ቦታ መውደቃቸው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ሲያረጋግጥ ነው። ሉሲ ከዚህ ነው የተገኘችው። የሰው ዘር ከዚህ ነው የተገኘው። ከኢትዮጰያ ነው የተገኘው። ስለዚህ ከኢትዮጵያ መገኘታቸውን ሲመሰከር ነው እግዚአብሄር በአንድ በኩል። ዛሬ እኛ በጎጥ ፣ በዘር፣ በጎሳ እንለያያለን፤ እንናቆራለን። ያን ሁሉ ሲመሰክርብን ነው እግዚአብሄር። የዓለም ህዝብ ግንዱ አንድ መሆኑን ሊመሰክርብን ነው ይህን ሁሉ ያደረገብን” ይላሉ። አቶ ባትሪም ለሌሎች ይመክራሉ። “ሰው እንዲህ እንደወጣ መቅረት መኖሩን አምኖ እርስ በርስ ከመናቆር አንድ መሆኑን አረጋግጦ፤ ከዛ ሁሉ እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ አማራ ነኝ፣ እኔ ትግሬ ነኝ፣ እኔ ጉራጌ ነኝ ከሚለው ከዛ ሁሉ ጭንቅላቱ ተመልሶ አንድ መሆኑን የአዳም ልጅ፣ የሔዋን ልጅ መሆኑን አምኖ አብሮ በሰላም እንዲኖር ነው የምንፈልገው”

ጊምቹዎቸም አሉ ‘ጾም ሆነብን እንጂ በሬ ልናርድ ነበር። አርባው ሲደረስ ግን ጾሙ ስለሚወጣ በደንብ ከብት ተዘጋጅቶ ቁርባናቸውን እናወጣለን’ በማለት ለሟቾች ያላቸውን ክብርና ፍቅር ገልጸውልኛል። የዓለም ሕዝብ የተሰዋባት ናት መታሰቢያ ማቆም እንደሚያስፈልጋትም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። ስፍራው መታሰቢያ ቆሞለት፣ መንገድም ተሰርቶለት እኛም ቁርባኑን በየዓመቱ የምንዘከርበት ቦታ ይሁንልን የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ሌላው የጊምቢቹ ወረዳ ማኅበረሰብ ጉዳይ የጎሳና ብሔር ልዩነት የማያደርግ ንጹህ ኢትዮያዊ ሰሜት ባለቤት መሆኑ ነው። ከመልካም ጎረቤቶች ድንበር ተሻግሮ ቤተሰብ ሆኖ መኖር እንደሚቻል ማሳያዎች ናቸው። 'ጋራ ቡካ' አማራና ኦሮሚያ ድንበር ላይ ያለ በደርግ ዘመን በተተከለ ባህር ዛፍ የተሸፈነ ተራራ ነው። ከጋራው በስተምዕራበ ኦሮሞዎች ጊምቢቹዎች ናቸው። በምስራቅ የምንጃር ሸንኮራ አማራዎች ናቸው። አቶ ባትሪ ለማ “ከሸንኮራዎች ጋር በሰላም ነው የምንኖረው፤ ፅብ የለም። ዛሬ ቀርቶ በኃይለስሴም በደርግም፣ በኢህአዴግም ነበርኩ እኛጋ ችግር የለም።ደርግ እነሱን ሲጨፈጭፍ ሴቶቻቸውን፣ ከብቶቻችውን እኛ ነን የተቀበልናቸው። እኛጋ ነው የሸሹት። አብልተን አጠጥተን ያኖርነው” ይናገራሉ። በማህበራዊ ኑሮ ረገድም “አጨዳ እንሄዳለን፤ እነሱ ይመጣሉ። አበልጀ አሁን ሸንኮራ ነው። ጋብቻ ሸንኮራ አለ። ምንጃር አለ። ተዋልደናል፤ ተፋቅረናል ልዩነት የለንም። ሰው ሰው ነው። እንኳን ኢትዮጵያዊ የዓለም ህዝብ ሰው ነው” በማለት የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌትነታቸን ይናገራሉ። ሁለቱ ጎረቤቶች ተረዳድተው ያርሳሉ፤ ተጠራርተው ያጭዳሉ፣ ሸንኮሬና ምንጃሬዎች ከጊምቢቹ ቆንጆዎች መርጠው ያገባሉ። ጊምቢቹዎች ጋሩ ቡካን አልፈው የምንጃርን ልጅ ያገባሉ። በአደጋ ጊዜ ይጠራራሉ። ወረዳው ከወረዳ፣ ሚሊሻው ከሚሊሻ በጸጥታ ጉዳይ እንደሚወያይ ነዋሪዎቹ አረጋግጠውልኛል። አዲስ ክስተት ቢፈጠርም ወዲያወኑ ተነጋግሮ ይፈታል እንጂ ምንም የሚፈጠር ግጭት አይኖርም ይላሉ። “ጋብቻም ነን። ድምበርተኛ ነን። ኑሯችን አብሮ ነው፤ ግጭት የለንም። እንረዳለን፣ እንሄዳለን እንመጣለን። ዕድርም አብረን እንጠጣለን” ያሉኝ የስፍራው አርሶ አደር ይሄ በሃሳብ ሳይሆን እርሳቸው የሚኖሩት መሆኑን ያረጋግጣሉ። “እኔም ከዛ ነው ያገባሁት። ብዙ ወልዳልኛለች። የመነጣጠል ሰሜት የለንም። እግዚአብሄር እንዳይነጣጥለን ነው የማመሰግነው” በማለት ነበር ሀሳባቸውን ሳይሆን ኑሯቸውን የነገሩኝ። አማራና ኦሮሚያ ለማለት ‘ክልል 3 እና 4' እያሉ የሚጠቀሙት ጊምቢቹዎች ከምንጃር ሸንኮራዎች ጋር ባላቸው ሁሉን አቀፍ የጋራ ጉርብትናና ቤተሰባዊ ግንኙነት የከሰሩበት ቅንጣት ነገር አላገኙም። ዛሬ በአማራና ኦሮሞ ሊሂቃን መካከል በሚደረግ እሰጣገባ ግን ታሪካዊቷን አገር ለማፈራረስ ስጋት ደቅኗል። ዳሩ እንዲህ አይነት ፍፁም ደጋግና ፍቅር ካለበት የገጠር መንደር ለድንገት ሲገኙ ስለ አገር ያንዣበበው አደጋ ስጋት በቅጽበት ብንን ብሎ ይጠፋል።

በቁርባን ስነ ስርዓቱ ድንገት ከተገኙ ሰዎች መካከል አንዱ የግል አብራሪና የሮሪድ ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወጣት ዮናታን መንክር አንዱ ነው። ዮናታን ወደ ጊምቢቹ ያቀናው የኀዘን ስነ ሰርዓት መኖሩን ሰምቶ አይደለም፤ ከአንድ ጓደኛው ጋር ኀዘኑን በስፍራው ለመግልጽ እንጂ። ከኢጀሬ ከተማ ታጥፎ ወደ አደጋው ስፍራ ሲያቀና መንገድ ላይ ነው ስለመርሐ ግብሩ የሰማው። እህል፤ውሃ ይዘው ወደ መርሐ ግብሩ በእግራቸው የሚኳትኑ ሰዎች ጋር ተገናኘ። ስለዝግጅቱ ብቻ አይደለም ያጫወቱት። ከያዙት ስንቅ ካልቀመስህ እያሉም አስቸግረውታል። በኢጀሬ የዘመድ ለቅሶ ያለባቸው ሁሉ ለቅሷቸውን ትተው 'በአንድ አውሮፕላን ያለቁ ሰዎች ጉዳይ ይበልጣል' በሚል ወደ ስፍራው መሄዳቸው አስገርሞታል።

"ሰባዕዊነትን በህይወት ከምትረዳበት አጋጣሚዎች አንዱ ይሄ ነው" የሚለው ዮናታን ሰዎቹ ማንም ሰው ሳይቀሰቅሳቸው፣ ለይምሰል ሳይሆን የሚኖሩትን ማድረጋቸው ዓለም ድንበር አልባ መሆኑን፣ ሰብዓዊነትም ድንበር እንደሌለው ማሳያ መሆኑን ይናገራል። "ይህ አደጋ ኢትዮጵያ ባለችበት ወቅታዊ ሁናቴ ብዙ የሚያስተምር ክስተት ነው" ብሏል ዮናታን። የከተማ ሰው ቢሆን ሰው ሞቶ ቢያ ፎቶ አንስቶ ሶሻል ሚደያ ላይ ይለጥፋል እንጂ እንዲህ አይነት ሰባዕዊነት እንደሌለው ያስረዳል። "ከተሜዎች ከባሕላችን፣ ከኅብረተሰባችን መማር ይገባናል፤ የሰባዊነት ጥጉን የምታይበት ማህበረሰብ ነው ያለው" ብሏል። ስለሞቱት ሰዎች ማንነት የማያውቁ የአካባቢው ነዋሪዎች አድራጎት የኀዘናቸውን ብርታት ማሳያ እንደሆነ ይገልጻል። "ከከተማ ወጣ ብለህ ስታይ አገራችን ምንም እንደማትሆን ተስፋ ይሰጥሃል። በሕዝባችን ሰባዕዊነት ተጽናናቻለሁ፣ ተደስቻለሁ። ምንም ብናደርግ አገራችንን ሊጠብቅ የሚችል ሕዝብ እንዳለ ተረድቻለሁ። ሊያርመን፣ ሊያተካክለን ይገባል" ነው ያለው ዮናታን።

የአደጋ ቦታው የአየር ትራንስፖርት ወይም አቬሽን ዘርፉን ቀይሯል። የቦይንግ 737 አውሮፕላን ተጠቃሚ 50 አገራት በረራ አግደዋል። የአሜሪካው አምራች ድርጂቱ ወጥረት ውስጥ ገብቷል። በስድስት ደቂቃ ልዩነት የማይተዋወቁ ዓለሞች ተገናኝተዋል። እናም ይህ ቦታ መታሰቢያ እንደሚያስፈልገው ዮናታን አይጠራጠርም። "ህብረተሰቡ ያሳየው ሰባዕዊነት ከመታሰቢያ ባሻገር የሰብዓዊነት ምልክት ሊቀመጥለት ይገባል። የኛ የአንድነታችን ምልክት ነው። የሰው ልጅን ፍቅርና ሰባዕዊነት የሚገልጽ እንጂ ተራ መታሰቢያ አይደለም መቆም ያለበት" ብሏል የግል አብራሪው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም