ቀጥታ፡

"ሕገ መንግስቱ ግንቦት 20 ካጎናጸፈን ድሎች መካከል ዋነኛው ነው"-አምባሳደር ሙሉጌታ ኃይሌ

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 "የሕገ መንግስቱ መደንገግ ግንቦት 20 ካጎናጸፈን ድሎች መካከል ዋነኛው ነው" ሲሉ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉጌታ ኃይሌ ገለጹ። በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 27ኛውን የግንቦት 20 በዓል በካርቱም በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል። አምባሳደር ሙሉጌታ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሕገ መንግስቱ ግንቦት 20 “ካጎናጸፈን ወሳኝ ድሎች ውስጥ በቅድሚያ የሚጠቀስና ዋነኛው ነው።” በዚህ ረገድም ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ህዝቦች "ጥቅማችን ተነክቶብናል፤ በህገ ወጦች ተወረናል" ብለው በየማዕዘኑ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ ሕገ መንግስቱን ተንተርሰውና በሰላማዊ መንገድ ሲያቀርቡ እንደነበር ተናግረዋል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም አገሪቷ ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታና ራሱን ገምግሞ ለችግሩ መፍትሔ ናቸው ያላቸውን መሰረታዊ እርምጃዎች በመውሰድ አሁን አገሪቷ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለሷን አመልክተዋል። “እኛም ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርገን በሱዳንና በሌሎች አገራት የሚኖሩ ዜጎቻችንን የማገልገል ግዴታ እንዳለብንና በአገሪቷ በህጋዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን መብት እንዲጠበቅ መንግስት እንደሚሰራ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉም ነው አምባሳደር ሙሉጌታ የተናገሩት። "አሁን ያለችው ኢትዮጵያ የግንቦት 20 ፍሬ ነች፤ የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት አሁን በዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ አስር አገሮች ተርታ ውስጥ የምትሰለፍ አልነበረችም፤ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣ በማህበራዊውም በሁሉም መለኪያዎች አሁን ያለችው ኢትዮጵያ አልነበረችም" ብለዋል። የአሁኑ ድል የተገኘው ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሎበት እንደሆነና ይህን የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው “እዚህ ላደረሱን ሰማዕታት ክብር” እንደሚገባቸውና ሁሌም ሲታወሱም እንደሚኖሩ አስታውቀዋል አምባሳደሩ። በዓሉ የድል በዓሉን በሚያስታውሱ ግጥሞችና የኢትዮጵያን ባህል በሚያሳዩ ጭፈራዎች መከበሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም