የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ለሞቱ ዜጎች ጸሎት አደረጉ

81

አዲስ አበባ  መጋቢት 12/2011 የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ለሞቱት የጸሎት ስነ ስርዓት ወይም ስርዓተ ቁርባን አደረጉ።

ነዋሪዎቹ "በስፍራው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን በማንነታቸው ባናውቃቸውም ሰው በመሆናቸውና እኛም ሃዘን ስለተሰማን የቁርባን እና የጸሎት ስነ ስርዓት አድርገናል" ብለዋል።

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 የበረራ ቁጥር ኢቲ 302  ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ሲከሰከስ 149 ተሳፋሪዎችና 8 የበረራ ሰራተኞች በድምሩ 157 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

በዚህም በምስራቅ ሸዋ ዞን የጊምቢቹ ወረዳ ነዋሪዎች አደጋው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ሃዘናቸውን ሲገልጹና ለስፍራው ጥበቃ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ በአካባቢው ኃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት መሰረት ሰው በሞተ በ12ኛ ቀን የሚፈጸመውን ስርዓተ ቁርባን ህይወታቸው ላለፈው ሰዎች አድርገዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በአደጋው የሞቱት ዜጎች የእኛው አካል ስለሆኑ በባህላችን መሰረት ጸሎቱን ለማድረግ ወስነናል ብለዋል።

የአካባቢው እናቶች በባህሉ መሰረት ለቁርባን ስርዓት ጸሎት የሚሆን ምግብና መጠጥ አዘጋጅተው በቦታው አቅርበዋል። ''የወደቁ ወገኖቻችንን ለማስታወስ በፈቃዳችን ያደረገነው ነው'' ብለዋል።

በአውሮፕላኑ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች አደጋው የደረሰበት ማህበረሰብ ሃዘኑን ሲገልጽና ህይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦችም በስፍራው በመገኘት እርማቸውን ሲያወጡ ቆይቷል።

በደረሰው አደጋ የ 35 አገሮች ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም