አየር መንገዱ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ቀጥታ በረራ ይጀምራል

123

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጪው ሚያዝያ አንድ ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

አየር መንገዱ ወደ ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ መጀመሩ በአውሮፓ ያለውን መዳረሻ ወደ 19 ከፍ ያደርግለታል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ''ወደ ኢስታንቡል የሚጀመረው በረራ አፍሪካን ከአውሮፓ በማገናኘት ለአየር መንገዱ ደንበኞች ሌላ የግንኙነት አማራጭ ይሆናል'' ብለዋል።

ፈጣን የኢንዱስትሪ ዕድገት እያስመዘገበች  ባለችው ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ መደረጉ የሕዝብ ለሕዝብ እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያስችል መግለጻቸውን አየር መንገዱ ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያሳያል።

አየር መንገዱ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ የሚያደርገው በሳምንት ሶስት ቀናት ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁን ጊዜ 119 ዓለምዓቀፍ የበረራ መዳረሻዎች ሲኖሩት ወደ አውሮፓ አገሮችም በሳምንት 57 ጊዜ ይበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም