ኢንስቲትዩቱ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ለተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ለተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የኩፍኝ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማከናወኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን 11 ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሓረርጌ ዞን 4 ወረዳዎች፣ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን 2 ወረዳዎች በአጠቃላይ በ17 ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች መከሰቱን በመግለጫው ተገልጿል።
በሶማሌ ክልልም እንዲሁ በ8 ዞኖች በሚገኙ 41 ወረዳዎች መከሰቱን በመጠቆም ይህንን ተከትሎም የየክልሎቹ ጤና ቢሮዎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ቅድመ ምላሽ መስጠታቸውን ያብራራው መግለጫው ወረርሽኙን በዘላቂነት ለማስቆምን የኩፍኝ መከላከያ ክትባትና የስራ ማስኬጃ በጀት ጠይቀዋል።
በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ለ800ሺህ45 ህጻናትና ታዳጊዎች የሚሆን የክትባት አቅርቦት የተደረገ ሲሆን በሶማሌ ክልልም እንዲሁ ለ133ሺህ838 ዜጎችም የክትባት አቅርቦት መደረጉም በመግለጫው ተካቷል።
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የወረርሽኙን ክትባት በመስጠት ላይ እንደሆነ ጠቁሟል።
በሽታው በትንፋሽ፣ በማስነጠስና ከአፍና ከአፍንጫ በሚወጣ ፈሳሽ አማካኝነት በቀላሉ የሚተላለፍ መሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰራጭ እንዳደረገው ተገልጿል።
ለነዚህ አጋላጭ መንስኤዎችም ክትባት ያልተደረገላቸው ህጻናት በስፋት መኖራቸውና ታመው ህክምና ከተደረገላቸው ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ መደበኛ የኩፍኝ ክትባት ተከትበው የማያውቁ በመሆናቸው እንደሆነም ተጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅትም በኢንስቲትዩቱ የሚመራ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዓለም የጤና ድርጅት፣ ከዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ከህጻናት አድን ድርጅትና ከኤም.ኤስ.ኤፍ በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ የተውጣጣ የሃኪሞችና የክትባት ባለሙያዎች ቡድን ወደስፍራዎቹ በማቅናት ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።
በዚህም እድሚያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ በኦሮሚያ ክልል 778ሺህ553 እና በሱማሌ ክልል ደግሞ 133ሺህ838 ዜጎች ክትባት ለመስጠት ጤና ሚኒስቴር ለመደበኛ ክትባት ከያዘው የመጠባበቂያ ክምችት 961ሺህ455 የክትባት መድሃኒቶች ወጪ ተደርጓል።
መስከረም 2011 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ ክትባቱ መሰጠቱን መግለጫው አስታውሷል።