የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ፊደል ቀረጻና ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት በፖሊሲ ሊታገዝ ይገባዋል ተባለ

195
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርትና ፊደል ቀረጻ በፖሊሲና በማዕከላዊ አሰራር መደገፍ እንዳለበት ተጠቆመ። የኢፌዴሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ ጋር ባዘጋጁት መድረክ  በሀገሪቷ ወጥነት ያለው የቋንቋ አጠቃቀምና ጽሕፈት እንዲኖር ያለመ መድረክ ተዘጋጅቷል። ዛሬ በአዲስ አበባ በተሰናዳው በዚህ መድረክ ላይ በርከት ያሉ ምሑራን ጥናታቸውን አቅርበው፤ ውይይት ተደርጓል። በመሆኑም በኢትዮጵያ አሁን እየተስተዋለ ያለውን የተዘበራረቀ የቋንቋ ስርዓተ ጽሕፈት ለመፍታት የሚያስችሉ ግብዓቶችና ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። ስርዓተ ጽሕፈት በማዘጋጀትና ማሻሻልን በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም አማርኛንና ሌሎች የሀገሪቷ ቋንቋዎች ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችና ዝግጅቶች በጥንቃቄና በፖሊሲ ታግዘው መከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አሁን ላይ በሀገሪቷ "ከ 52 በላይ ቋንቋዎች ስርዓተ ጽሕፈት ተዘጋጅቶላቸዋል" ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ስርዓተ ትምሕርቱ ሲዘጋጅ የሄዱበትና የተከወኑበት መንገድ ግን ዝብርቅርቅ ያለ ነበር ብለዋል። ያበመሆኑም የቋንቋው ባለቤቶች ሳይካተቱ በሌሎች አካላት ስርዓተ ትምሕርት እንደተዘጋጀላቸው ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የስርዓተ ትምሕርት ዝግጅት በአሰራርና በፖሊሲ መዘጋጀት አለበት ሲሉም አሳስበዋል። በፊደል ቀረጻና መዛግብተ ቃላት በማዘጋጀት ረገድ፤ አሁን ላይ በሀገሪቷ ካሉ ስርዓተ ትምሕርት ከተቀረጸላቸው 52 ቋንቋዎች ውስጥ 12ቱ ብቻ የኢትዮጵያን ፊደል እንደሚጠቀሙ እና 40 ያሕሉ የላቲን ፊደልን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ። ለዚህም በርከት ያሉ ምክንያቶችን የሚጠቅሱት ዶክተሩ፤ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂያዊ ምክንያቶች ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ  የቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ ምክትል ዳሬክተር ዶክተር ተሾመ  የኋላሸት በበኩላቸው ፊደል ማሻሻልና መቀየር በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እጅግ ፈታኝና ጥንቃቄን የሚፈልግ ጉዳይ ነው ይላሉ። "ፊደል ታሪክ ነው፤ ፊደል ማንነት ነው" የሚሉት ዶክተር ተሾመ፤ ቋንቋን በማሻሻልና በመቀየር ረገድ የድሮውን ታሪክ የሚያሳጡና የቀደመ እውቀትና ጥበብን የሚያሳጡ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ በማለት አስረድተዋል። እንዲያውም ይላሉ ዶክተር ተሾመ፤ ፊደልን ማሻሻል አጅግ ፈታኝ በመሆኑ ምክንያት በሀገሪቷ በርከት ላሉ ዓመታት የአማርኛን ስርዓተ ጽሕፈት ለማሻሻል ተሞክሮ አከራካሪና አጨቃጨቂ  ጉዳዮች በመፈጠራቸው ምክንያት አልተሳካም ይላሉ። ባይሆን ከዚህ በኋላ የሚደረጉ የስርዓተ ትምሕርት ዝግጅቶችና ፊደል ቀረጻዎች ስነ ልሳናዊ፤ ታሪካዊና ስነ ልቦናዊ ይዘቱንና ሙያዊ መሰረቱን ይዘው መከናወን አለባቸው ሲሉም አስገንዝበዋል። አሁን ላይ "የቋንቋ ስርዓተ ጽሕፈትና ይዘት ማሻሻያ ይደረግልን" የሚሉ ጥያቄዎች  እየተሰኑ ነው ያሉት ደግሞ በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋዎችና የባሕል እሴቶች ዳይሬክተር አቶ አለየሁ ጌታቸው ናቸው። እንደ አቶ አለየሁ ገለጻም በኢትዮጵያ የስርዓተ ጽሕፈት ቋት ለማዘጋጀትና በፖሊሲና በሙያ ለመደገፍ እየተሰራ ነው ብለዋል። የየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ማሕበረሰብ ስርዓተ ጽሕፈቱን ለማሻሻል በሚፈልግበት ጊዜ አማራጭ የስርዓተ ጽሕፈት ቋት ተዘጋጅቶ፤ ወጥነት ያለው አጻጻፍና ንባብ እንዲኖር  ለማድረግም  ስራ ላይ ነን ብለዋል። ስርዓተ ጽሕፈትን ማሻሻል በበርካታ ሀገራት አንደታየው  "የሚቻል አይደለም" የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ ገና ስርዓተ ትምሕርታቸውን በቋንቋቸው ያላዘጋጁ ስርዓተ ጽሕፈቱን እንዲያውቁና ወጥነት እንዲኖር ማድረግ ግን እንደሚቻል ያወሳሉ። በርካታ ታሪክ የተጻፈባቸውን ነባር ቋንቋዎችን ማሻሻል ከባድ ነው ሲሉም አቶ አለማየሁ አጽንኦት ሰጥተው ያብራራሉ። በላቲንና በኢትዮጵያ ፊደል አጻጻፍ፤ የስነ ድምጽና ስርዓተ ጽሕፈት መረጃዎችን  ሰብስቦ በማከማቸትና  አማራጭ እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዝ መረጃ የሚይዝ ነው ቋቱ። በመሆኑም በቀጣይ የቋንቋዎችን ስርዓተ ጽሕፈት በተሻለ መልኩ ለማገዝ እንዲቻል  የቋንቋ ፖሊሲ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ሲገባ ችግሩን ይፈታል ይላሉ አቶ አለማየሁ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም