በትግራይ ክልል በግብር አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ

መቀሌ ግንቦት 23/2010 በትግራይ ክልል ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ ጋር ተቀራርቦ በመወያየት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ። በክልሉ በመጪው ክረምት የሚጀመረውን ግብር የመሰብሰብ ሥራ ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በመቀሌ ከተማ ውይይት ተካሄዷል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አዲስአለም ባሌማ እንዳሉት፣ በግብር አሰባሰብ ሥራ ላይ ግልጽና ፍትሃዊ አሰራርን ማስፈን ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህም በዘርፉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት። ዶክተር አዲስአለም እንዳሉት ቀደም ሲል ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ የተለያዩ ግብር ከፋዮች ላይ የተለያየ ግብር የሚተመንበት ሁኔታ ነበር። ከግብር አተማመን ጋርም “ገልጽነት የለም” በሚል ከሕብረተሰቡ ቅሬታ ይነሳ እንደነበር አስታውሰው ይህንና በግብር አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ መሰል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከግብር ከፋይ ሕብረተሰብ ጋር በመወያየት መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል። የውይይት መደረኩም በግብር አሰባሰብ ሥራው ላይ በሚስተዋሉና በግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ ቅሬታን እየፈጠሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተለይተው በመፍትሄና መሰል ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ እንደሚያስችል አመልክተዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን የዓዲ-ረመጽ ወረዳ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ደጀን እንደገለጹት፣ ግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ ግብር የሚከፍለው አገራዊ ግዴታው ስለሆነ መሆኑን አስቀድሞ የማሳመን ሥራ ሊሰራ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በተለይ የመንግስትን ግብር የሚሰበስቡ አካላት ይበልጥ ተኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። በግብር አሰባሰብ ሥራ ላይ ከህዝቡ ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ፍትሃዊ የግብር አከፋፈል ሥርአት እንዲኖር እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ሀውዜን ወረዳ የገቢዎች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዝመራ ወልደማርያም ናቸው። በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የሰሀርቲ ሳምረ ወረዳ ገቢዎች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ግርማይ በበኩላቸው፣ በተሃድሶው የተለዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይደገሙ አስቀድሞ ትኩረት መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። በወረዳቸው ከገቢ ግብር አሰባሰብ ጋር እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ለሕብረተሰቡ በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ ከወዲሁ ለመስራት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል። የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልደገብርኤል አጽብሃ በበኩላቸው በክልሉ ህጋዊ የንግድ አሰራር እንዲጎለብት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በግብር አሰባሰብ ሥራው ላይ ህግና ስርዓት የሚከበረው ህጋዊ የሆነ አካሄድና አሰራርን መከተልና ህጋዊ ደረሰኝ የመቀበል ልምድ እንዲኖር ማድረግ ሲቻል በመሆኑ ለዚህ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው የገለጹት። በውይይት መድረኩ በክልሉ የሚገኙ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የገቢዎች፣ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም