ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዲስ የቦርድ አባላት ሹመትን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዲስ የቦርድ አባላት ሹመትን አጸደቀ
አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቦርድ አባላትን ሹመት አፀደቀ።
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቅራቢነት የተዘረዘሩትን የቦርድ አባላት ሹመት ነው ዛሬ ያጸደቀው።
በዚሁ መሰረት
1. አቶ ፍቃዱ ተሰማ - ሰብሳቢ
2. አቶ ተፈራ ደርበዉ- አባል
3. ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ- አባል
4. ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ- አባል
5. ዑስታዝ አቡበከር አህመድ - አባል
6. ዶክተር አብዲዋስ አብዱላሂ - አባል
በመሆን የተሾሙ ሲሆን ቀደም ሲል የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አባላት የነበሩት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና ወይዘሮ ካሚላ ጁንዲ በአባልነታቸው እንዲቀጥሉ ተወስኗል።
ሹመቱ የምክር ቤቱ አባላትን ያከራከረ ሲሆን የሥራ መደራረብ፣ በዘርፉ ያላቸው የትምህርት ዝግጅት እና የኃይማኖት ሰዎችን በቦርድ አባልነት ማምጣት የመንግስትና ኃይማኖት ድንበርን የጣሳ ነው የሚሉ ኃሳቦች ተነስተው እንደገና ታይቶ ቢመጣ የሚሉ አስተያየቶችም ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።
ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ አባላት የቀረበውን የውሳኔ ኃሳብ በ10 ተቃውሞ በ28 ድምፀ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አመራር አባላትን ሹመት አጽድቀውታል።
ሹመቱ ኮርፖሬሽኑን እንደገና ለማደራጀት በወጣው አዋጅ ቁጥር 858/2006 አንቀጽ 7 እና 8 መሰረት የተፈፀመ መሆኑም ተገልጿል።