የኔትዎርክ መጨናነቅን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት በቦታ እጦት ምክንያት እየተስተጓጎለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኔትዎርክ መጨናነቅን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት በቦታ እጦት ምክንያት እየተስተጓጎለ ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011በአዲስ አበባ ከእጥፍ በላይ የጨመረውን የቴሌኮም ኔትዎርክ መጨናነቅ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት በቦታ እጦት ምክንያት እየተስተጓጎለ መሆኑን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ።
የቴሌኮሙ የኔትዎርክ ዲቪዥን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ኃይለመስቀል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤ በከተማዋ ያለው የኔትዎርክ መጨናነቅ ባለፉት ስድስት ወራት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።
በተለይም ኢትዮ-ቴሌኮም በኢንተርኔትና በድምፅ ጥቅል አገልግሎት ላይ የታሪፍ ቅናሽ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ አገልግሎቱ ከ30 ቴራ ባይት ወደ 62 ቴራ ባይት መጨመሩን ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ይህን ተከትሎ በተለይም ሁለተኛ ትውልድ ተብሎ በሚጠራው /2G/ እና በሦስተኛው ትውልድ /3G/ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ የኔትዎርክ መጨናነቅና መቆራረጥ እያጋጠመ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም ሳቢያ በአንዳድ አካባቢዎች፣ ቢሮዎችና መኖሪያ ቤቶች በሚደረጉ የድምፅና ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎቶች ላይ የጥራት ችግር ይታያል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ይህንን ችግር ለመፍታት በከተማዋ የተመረጡ ስምንት አካባቢዎች መለየቱ ተገልጿል።
በተለዩት አካባቢዎችም የኔትዎርክ ማስፋፊያ መሳሪያዎችን ከውጭ አስገብቶ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ቢያደርግም ከተለዩት ስምንት አካባቢዎች ሥራውን ለመጀመር ፈቃድ የተገኘው ሁለቱ ቦታዎች ብቻ ናቸው።
ቀሪዎቹ ስድስት ቦታዎች በግለሰቦች የህንፃ ጫፍ ላይ የሚገኙ በመሆኑና የሕንፃ ባለቤቶቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማስፋፊያውን ማከናወን እንዳልተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል።
በሌሎች አገራት ለህዝብ ጥቅም የሚውሉ የማኅበራዊና የመሠረተ-ልማት አገልግሎቶችን ለማከናወን የኔትዎርክ ማስፋፊያ ቁሳቁሶችን በግለሰቦች የሕንፃ ጫፍ ላይ መትከል የባለቤቶቹ ፈቃድ ግዴታ መሆኑ በህግ ተደንግጓል።
በኢትዮጵያ መሰል አስገዳጅ ሕግ ባለመኖሩ የማስፋፊያ ሥራውን አስቸጋሪ አድጎታል ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ።
በዚህም ምክንያት ስድስቱ ቦታዎች ለመትከል የተገዙት የኔትዎርክ ማስፋፊያ ቁሳቁሶቹ ያለአገልግሎት ተቀምጠው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በኢትዮጵያ ለህዝብ ጥቅም የሚውሉ የኔትዎርክ ፕሮጀክቶችን በግለሰብ ህንፃ ላይ ለመትከል የሚያስገድድ ህግ መኖር አለመኖሩን ከአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ አጣርቷል።
የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው "እንደሌሎች አገራት ለህዝብ ጥቅም የሚያውሉ ልማቶችን በግለሰብ ቦታ ወይም ህንፃ ላይ ለመገንባት የሚያስችል የግንባታ አስገዳጅ ህግ የለም" ብለዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮ-ቴሌኮም ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ቢያቀርብ ለባለሀብቶቹ የትብብር ደብዳቤ በመፃፍና በመግባባት መስራት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም የማስፋፊያ ሥራውን ለማከናወን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቦታ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ እስካሁን ከአስተዳደሩ ፈቃድ የተገኘባቸው ሁለቱ ብቻ ናቸው።
አገልግሎቱን ለማከናወን ፈቃድ የተገኘባቸው በጀሞ ኮንዶሚኒየምና በዓለም ገና አካባቢ የሚገኙት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጀመሩን ኃላፊው ተናግረዋል።