˝ የአንድነትና የሰላም ድልድይ ግንባታ˝ ጉባኤ በለንደን ተካሄደ

101

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት 'የአንድነትና የሰላም ድልድይ ግንባታ' ጉባኤ በለንደን ተካሄደ።

ጉባኤው የተካሄደው ባለፈው መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓም በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ  መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል።

ጉባኤው በኢትዮጵያውያን መካከል የበለጠ መተማመንና መረዳዳትን ለማስረጽ፣ ጥላቻን ለመናድና በአገራቸው ጉዳይ በያገባኛልና በባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ሃሳብ ለመለዋወጥ ያለመ ነው ተብሏል።

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍስሃ ሻውል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሂደት ላይ ነች፤ ለዚህ ለውጥ ቀጣይነት ደግሞ ዳያስፖራው የማይተካ ሚና አለው።

ኤምባሰው ከሁሉም ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጋር ተባብሮ ለመስራትና ለማገልገል ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን፤ ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤም የዚህ ቁርጠኝነት ጅማሬ እንደሆነም ገልፀዋል።

በእንግሊዝ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በገጽታ ግንባታና መሰል ዘርፎች የአገራቸው አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤምባሲውም ዜጎች ለሚፈልጉት ሁሉንም አይነት አገልግሎት ለመስጠት ሁሌም በትጋት ለማገልገል መዘጋጀቱን አምባሳደር ፍስሃ ገልጸዋል።                          

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም