ዐቃቤ ህግ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ የመሠረተውን ክስ አሻሽሎ አቀረበ

95

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ የመሰረተውን ክስ አሻሽሎ አቀረበ።

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ዛሬ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 5ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ዐቃቤ ህግ ከዚህ በፊት በአቶ ኢሳያሰ ዳኘው ላይ የመሠረተው ክስ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 33 መሠረት በልዩ ወንጀል ተካፋይነት እንዲሁም በአንቀጽ 411 የመንግስትን ስራ በማያመች መልኩ በመምራት ብሎ ያቀረበውን የክስ ጭብጥ አሻሽሏል።

በዚህ መሠረት ክሱ ''በአንቀጽ 32 በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በአንቀጽ 407 ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል ወንጀል'' በሚል የተሻሻለ መሆኑን ዐቃቤ ህግ አስረድቷል።

ተከሳሽ ስልጣናቸውን በመጠቀም ለራሳቸውና ዜድቲኢ (ZTE) ለተባለ ኩባንያ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ ያለ ግልጽ ጨረታ በመመሳጠር ከኢትዮ ቴሌኮም የግዢ መመሪያ ውጭ ለዩኒቨርሲቲዎች የኔትወርክ ዝርጋታ አገልግሎት የሚውል የ44 ሚሊዮን 510 ሺህ 971 ዶላር ወይም 768 ሚሊዮን 704 ሺህ 469 ብር ከ17 ሳንቲም ግዢ በመፈጸም በመንግስትና በህዝብ ላይ ጉዳት ያደረሱ መሆኑን ዐቃቤ ህግ ያሻሻለው የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ አቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ ተሻሽሎ የቀረበውን ክስ ለተከሳሹ በጽሑፍ እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን የክስ መቃወሚያቸውን  ለመጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ. ም እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም