በአዳማ ከተማ ከ660 ሺህ በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

92

አዳማ  መጋቢት 10/2011 በአዳማ ከተማ ከ660 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ዲቭዥን ኃላፊ ኮማንደር ዲኖ ኢማም ለኢዜአ እንደገለጹት የኮንትሮባንድ ዕቃው ሊያዝ የቻለው ከሕብረተሰቡ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ነው። 

የኮንትሮባንድ ዕቃው በትናንትናው ዕለት በህዝብ ትብብር የተያዘው በአዳማ ደምበላ ከፍለ ከተማ ደጋጋ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቀጠና ሦስት እየተባለ በሚጠራ አካባቢ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው።

"ከተያዙት ዕቃዎች መካከል ዘመናዊ የሞባይል ቃፎዎች፣ ሳታላይት ዲሽና አንቴናዎች፣ የሞባይል ባትሪድንጋይ፣ ዲኮደሮች፣ የተለያዩ ሽቶዎችና የኤሌክትሮንክስ እቃዎች ይገኙበታል" ብለዋል።

ኮማንደር ዲኖ እንዳሉት የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች 667 ሺህ 445 ግምት ያላቸው ናቸው።

ዕቃዎቹ ተከማችተው የተገኙባቸው ተጠርጣሪ ግለሰብ አቶ ሙሐመድ ከድር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የተያዘው እቃ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን አዳማ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉንም ኮማንደር ዲኖ አመልክተዋል።

ህግ ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የከተማዋ ሕብረተሰብ እያደረገ ያለውን ተሳትፎና ትብብር ይበልጥ እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም