ቢሮው በ176 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ወርክሾፖችን እያደራጀሁ ነው አለ - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው በ176 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ወርክሾፖችን እያደራጀሁ ነው አለ
አዳማ መጋቢት 10/2011 በክልሉ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት በ176 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ወርክሾፖችን እያደራጀ መሆኑን የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቢሮው በክልሉ 21 ኮሌጆች የሚሰጠውን ትምህርት ምሉዕነቱን ለማረጋገጥ ወርክሾፖቹን በዘመናዊ መልኩ እያደራጀ ነው።
እስካሁን ወርክሾፖቹ በ16 ኮሌጆች መደራጀታቸውንም አስታውቀዋል።
ወርክሾፕ ኮሌጆቹ በንድፈ ሃሳብ ከሚሰጥ ስልጠና ወጥተው በተግባራዊ ትምህርትና ስልጠና ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋሉ ብለዋል።
የአገሪቱን ልማትና እድገት በዕውቀትና በፈጠራ ታግዞ ለማስቀጠልና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ስልጠናውን እያዘመንን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ቢሮው በአጫጭር ፣ መካክለኛና ረዥም የሙያ ስልጠና የሚወስዱ ሰልጣኞችን ብቃት ለማሳደግና በሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረቱን እንደሚያጠናከርም ገልጸዋል።
ኮሌጆቹ በምርምር የሚያወጡትን ቴክኖሎጂ ለማላመድና ለማስፋፋት ጥራት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መስጠቱንም ኃላፊው አስታውቀዋል።
ሰልጣኞች በሰለጠኑበት ሙያ ያላቸው ብቃት የመጀመሪያ ማረጋገጫ የትምህርት ጥራት አንዱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የካኔኑስ ኮሌጅ ዲን አቶ አድማሱ ድሪባ ናቸው።
ለዚህም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት በትምህርት ጥራት ላይ አተኩረው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን አቶ ተሾመ በቀለ በበኩላቸው በመማሪያ ቁሳቁስ የተደራጁ ተቋማት ሰልጣኞች የተሻለ ዕውቀትና ሙያ እንደሚያስጨብጡ ተናግረዋል።
ሰልጣኞች በሙያቸው ብቁ ሆነው እንዲወጡ የግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ኮሌጃቸው 70 በመቶ የተግባርና 30 በመቶ የንድፈ ሃሳብ ስልጠና በመስጠት ጥረቱን እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።