ቀጥታ፡

በትግራይ 293 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ በመፋጠን ላይ ነው ---የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን

መቀሌ 23/2010 በትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት በመደበው በጀት 293 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፓልት መንገድ ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ግርማይ ለኢዜአ እንዳሉት የመንገዱ ግንባታ የፌደራል መንግስት በመደበው ሦስት ቢሊዮን 820 ሚሊዮን ብር በጀት የሚካሄድ ነው። የመንገዱ ግንባታ በእቅዱ መሰረት ቀጥሎ በመፋጣን ላይ እንደሚገኝ አመልክተው ከዚህም ውስጥ የመቀሌ ፊናርዋ፣ ውቅሮ -ማይቅነጣል፣ ዓድዋ- ራማና አካባቢው እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ የአስፋልት መንገዱ በገጠር ሰባት ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆን፣ ከተሞችን አቋርጠው የሚያልፈው ደግሞ እስከ 30 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው አቶ አርአያ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛው የመንገዱ ግንባታ ከስምንት ወራት በፊት እንደተጀመረ የገለፁት አቶ አርአያ፣ የሚጠናቀቁበት ጊዜም በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የመንገዱ የአፈር ቆረጣ ስራዎች በአማካይ 60 በመቶ ያህሉ ተጠናቋል። የመንገዱ ተጠናቆ ላአገልገሎት ሲበቃ የአከባቢው አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ በቀላሉ እንዲያቀርቡ፣ የክልሉን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥራዊ የመስህብ  ስፍራዎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ማህበረሰብም የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ቁልፍ ሚና እንደሚነረውም አቶ አረአያ ገልጸዋል፡፡   የአስፋልቱ መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ያለው በአፍሮ ፅዮን፣ የሱርና የሃገር መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ነው። በመንገዱ ግንባታ ሂደት ከ1ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽ፣ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገብረኪሮስ ናቸው። "የአስፋልት መንገዱ ግንባታ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲፋጠንና በፀረ ድህነት ትግል ላይ የራሱን ሚና እንዲጫወት የስራ ተቋራጮች በጥራትና በፍጥነት ሊሰሩ ይገባል "ብለዋል። ከመንገዱ ግንባታ ጋር ተያይዙ ከመኖሪያ ቤትና የአትክልት ስፍራዎች የሚነሱ የካሳ ጥያቄዎች በወቅቱና በፍትሃዊነት ምላሽ እንዲፈቱ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። የመከላከያ ኮንስትራክሽን መቀሌ- ፊናርዋ መንግድ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመንፈስ ኪዳነ በበኩላቸው፣"ለህዝብና መንግስት ያለንን ታማኝነት በስራችን ለማረጋገጥ ዘመናዊ ማሽነሪዎችና ባለሙያዎችን አዘጋጅተን ሌተቀን እየተረባረብን ነን "ብለዋል። በትግራይ የነበለት ከተማ የልማት ኮሚቴ አስተበባሪ ሀጂ መስዑድ ዓብደርቃድር በሰጡት አስተያየት፣ የ30 ዓመታት የመንገድ ግንባታ ጥያቄ አሁን አውንታዊ ምላሽ አግኝቶ በህይወት እያሉ ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። ለዘመናት ሲቀርቡት የቆየው የመሰረተ ልማት ጥያቄ አሁን የመንግስት አዎንታዊ ምላሽ ማገኘቱ መልካም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ዋህድ ተክለሃይማኖት ናቸው፡፡ "በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ ደግሞ የበኩላችን ድጋፍ ለማድረስ ዝግጁ ነን" ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም