ቀጥታ፡

ዐቃቤ ሕግ በወይዘሮ ትዕግስት ታደሰ የዋስትና መብት ላይ ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አገኘ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2011 የፌዴራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀል በተከሰሱት ወይዘሮ ትዕግስት ታደሰ የዋስትና መብት ላይ ያቀረበው የይግባኝ ጥያቄ ተቀባይነት አገኝ።

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በፀሐፊነት ያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ ትዕግስት ታደሰ 'ከገቢ በላይ ሃብት በማካበት' በሚል የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሿ የመንግስት ሰራተኛ ሆና ሳለ ተቀጥራ ታገኘው ከነበረው ህጋዊ ገቢ የማይመጣጠን ምንጩ ያልታወቀ ሀብትና ንብረት በማፍራትና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስላ በመጠቀም እንዲሁም የቴምብር ቀረጥ ክፍያን በተገቢው መንገድ ባለመክፈል ወንጀል ዐቃቤ ህግ በተደራራቢ ወንጀል የከሰሳት ሲሆን ከወንጀሉ ክብደት አንፃር የዋስትና መብት እንዳይሰጣት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ተከሳሿ የሁለት ልጆች እናት፣ ቋሚ አድራሻ ያላት መሆኑዋ ከግምት ውስጥ በማስገባትና በተደራራቢ ወንጀል ብቻ በመከሰስ የዋስትና መብት ሊያስነፍግ የማይችል መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከሳሿ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ተለቃ የክስ ሂደቷን በውጭ ሆና እንድትከታተል ወስኖ ነበር።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመው ዐቃቤ ህግ ተከሳሿን በሙስና ወንጀል በአዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀፅ 5 መሰረት ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ይግባኝ በዛሬው እለት ተቀባይነት እንዳገኝ ገልጿል።

ተከሳሿ ወይዘሮ ትዕግስት ታደሰ ከዚህ በፊት በጀማ ሲሚኒቶ ፋብሪካ፣ በሸገር ሜትር ታክሲ፣ በሻግ አስመጪና ላኪ ድርጅት፣ በህብረት ባንክ አክሲዮን ማህበር ትሰራ የነበረ ቢሆንም ተከሳሿ ከነበረችበት የመንግስት ስራ እና በሌላ መንገድ ስታገኝ ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር ፍፁም የማይመጣጠን 7 ሚሊዮን 460 ሺህ 160 ብር ከ90 ሳንቲም በላይ የሚገመት ባለ ሶስት ፎቅ ቤት፣ ቶዮታ ላንድክሩዘር መኪና እንዲሁም ጥሬ ገንዘብ የተገኘባት መሆኑ ይታወሳል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ታደሰ የክስ መቃወሚያዋን በጠበቃዋ በኩል ያቀረበች ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎባታል።

በመሆኑም ዐቅቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያቀረበው የይግባኝ ጥያቄ ተቀባይነት በማግኝቱ የዋስትና ጥያቄው በስር ፍርድ ቤት የሚታይ ሲሆን ቀሪ የፍርድ ሒደቱ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ ነው ፍርድ ቤቱ ያመለከተው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም