በታንዛንያ እስር ቤት የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በታንዛንያ እስር ቤት የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 9/2011 በታንዛንያ ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እየተመለሱ መሆኑን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከታንዛንያ ማዌይኒ እስር ቤት ከተፈቱት 285 ዜጎች መካከል ከመጋቢት 6 እስከ 8 ቀን 2011 ዓ.ም 50 የሚሆኑት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
በዛሬው እለትም 40 ተጨማሪ ዜጎች ወደ አገራቸው እንደሚገቡ የሚጠበቅ ሲሆን እስከ መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ቀሪዎቹ እንደሚመለሱ የሚኒስቴሩ ምክትል ቃል አቀባይ አቶ አበበ መብራቱ ለኢዜአ ገልጸዋል።።
በታንዛንያ ዳሬሰላም ከሚገኙት ዩኮንጋና ሴጌሪያ እስር ቤቶች የተፈቱ ዜጎችም ወደ አገራቸው የመመለስ ስራ እንደሚሰራ በታንዛንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም)፣ከብሔራዊ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከታንዛንያ መንግስት ጋር በመተባበር ዜጎቹን የመመለስ ተግባር እያከናወነ ይገኛል።
እነዚህ ዜጎች ከእስር የተፈቱት የኢትዮጵያ መንግስት ከታንዛንያ መንግሥት ጋር በመነጋገር በምህረት የተፈቱ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
መንግስት በዚምባቡዌ ርዕሰ መዲና ሀራሬ በአስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያን እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ከተፈቱ በኋላም ወደ አገራቸው እንድመለሱ ይደረጋል ብለዋል።
እንደ አቶ አበበ ገለፃ በተለያዩ አገራት በእስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎችን በማስፈታት ወደ አገራቸው የመመለሱ ስራ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል።
በዚህ ዓመት በህዳር ወር መጨረሻ ላይ ከ230 በላይ ኢትዮጵያዊያን በታንዛንያ እስር ቤቶች ወደ አገር ቤት መመለሳቸው የሚታወስ ነው።