ቀጥታ፡

የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ በምስራቅ አፍሪካ ውድድር ሁለተኛ ሆኖ አጠናቀቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2011 በምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ።

የዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ውድድር ከመጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በዛንዚባር ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ተወክላለች።

ትናንት በፍጻሜው ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር ተጫውተው 30 ለ 17 መሸነፉን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ተሻላሚ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በምስራቅ አፍሪካ ዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር የተሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአጠቃላይ በውድድሩ ባስመዘገበው ውጤት መሰረት አምስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁንም አመልክተዋል።

ትናንት የዩጋንዳ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የኬንያ አቻቸውን 30 ለ 24 በማሸነፍ በሁለቱም የእድሜ ዘርፎች አሸናፊ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

27 ተጫዋቾችን ጨምሮ 33 ልዑካንን የያዘው የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ማታ ሁለት ሰዓት አዲስ አበባ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ኬንያ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በ2007 እና በ2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በ2009 ዓ.ም በጅቡቲ አዘጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም