16ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር መቐለ ሰብዓ እንደርታ ደደቢትን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል - ኢዜአ አማርኛ
16ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር መቐለ ሰብዓ እንደርታ ደደቢትን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል
አዲስ አበባ መጋቢት 8/2011 በ16ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ደደቢትን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ትናንት እና ዛሬ በክልል ከተሞችና አዲስ አበባ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል።
ትናንት በሊጉ መርሃ ግብር በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሀዋሳ ከተማን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።
በተመሳሳይ ዛሬ 9:00 ሰዓት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል የሊጉ አናት ላይ የሚገኘው መቐለ ሰብዓ እንደርታ ደደቢትን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍና ነጥቡን ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት ማጠናከር ችሏል።
ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0፣ ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 እንዲሁም ባህርዳር ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ዳግም 1 ለ 0 ማሸነፍ ችለዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ከአዳማ ከተማ 0 ለ 0 እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከስሁል ሽረ 1 ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።
በዚህም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከነበረበት 35 ነጥብ ወደ 38 በማሳደግ ነው በሊጉ መሪነቱን ማጠናከር የቻለው።
ፕሪሚየር ሊጉን መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ38 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲመራ፣ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ 2ኛ፣ ፋሲል ከነማ በ28 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በእኩል 26 ነጥብ 4ኛና 5ኛ ደረጃን ሲይዙ ባህርዳር ከነማ በ25 ነጥብ 6ኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ።
ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙና የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በተመሳሳይ 11 ግቦች ሲመሩ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ10 ግቦች ይከተላል።