ቀጥታ፡

መቀሌ 70 እንደርታ ደደቢትን 4 ለ1 አሸነፈ

መቀሌ/ጅማ መጋቢት 8/2011 በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ እግር ኳስ ውድድር መቀሌ 70 እንደርታ ደደቢትን 4 ለ1  አሸነፈ።

ጅማ አባጅፍር አዳማ ከተማን አስተናግዶ ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።

ዛሬ በትግራይ ዘመናዊ ስተድዮም በተካሄደው ውድድር ደደቢቶች መሪ ያደረጋቸውን ጎል በ47ኛው ደቂቃ ላይ በአለም ሳንታየሁ አማካኝነት አስመዝግበው ነበር ።

መቀሌ 70 እንደርታ በ52ኛ፣ በ55ኛ፣ በ70ኛና በ90ኛ ደቂቃዎች በተለያዩ ተጫዋቾች ባስቆጠራቸው አራት ግቦች ውድድሩን በበላይነት ሊያጠናቅቅ ችሏል ።

መቀሌ 70 እንደርታ ባስመዘገበው ውጤት 38 ነጥብ በመያዝ በፕሪሚየር ሊጉ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ደደቢት በበኩሉ ስድስት ነጥብ ይዞ መጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የመቀሌ 70 እንደርታ አስልጣኝ ገረመድህን ኃይሌ "ተጨወቾቻችን ለሁለት ሰምንት እረፍት ላይ በመቆየታቸው በመጀመሪያው 45 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዞ ነበር " ብለዋል ።

"በሁለተኛው 45 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ በመንቀሳቀሳቸው የጠበቅነውን ውጤት ልናስመዘግብ ችለናል"  ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ሚኪኤለ ገብረመስቀል በበኩላቸው "ውጤቱ በቀጣይ ያለብን ክፍተት አርመን እንድንመጣ ትምህርት ሰጥቶናል" ብለዋል ።

በሌላ ዜና ጅማ አባጅፋር ዛሬ በሜዳው ነጥብ ጥሏል፡፡

ጅማ አባጅፍር ዛሬ በ9፡00 ሰዓት አዳማ ከተማን አስተናግዶ ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡

የአዳማ ከተማ የአጥቂ መስመር ተጨዋች ብዙአየው እንደሻው የመጀመሪያ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት የጅማ አባጅፋር  የመስመር ተጨዋች በሆነው አስቻለው ግርማ ላይ በፈጸመው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባጅፋሮች ያገኙትን የሜዳቸውንና የተጫዋች ብልጫ ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡

ጅማ አበጅፋር በመከላከሉ በኩል የተሸለ ቢሆንም የመሀልና የአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾች ከፍተኛ የመናበብና ተደራጅቶ የመጫወት ክፍተት ታይቶባቸዋል፡፡

በጎዶሎ የተጫወተው አዳማ ከተማ በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ሙከራ ማድረግ የቻለ ቢሆንም በጅማ አባጅፋር በረኛ ጥረትና በቃት ከሽፎበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም