በጋሞ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ውስጥ በደራሽ ውሃ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

306
አርባምንጭ ግንቦት 23/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ትናንት በጣለው ከባድ ዝናብ ሁለት ወንዞች በደራሽ ውሃ  ሞልተው ባስከተሉት አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፋን የወረዳው ዋና አስተዳደሪ አስታወቁ። አስተዳዳሪው አቶ ጥላሁን ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው መካከል  በቦራዳ ቀበሌ ከክሾ ወንዝ ዳርቻ የነበሩ የስድስት እና የስምንት ዓመት እድሜ ያላቸው የአንድ ቤተሰብ ልጆች በደራሽ ውሃ  የተወሰዱ ይገኙበታል። እንዲሁም የ52 ዓመት እድሜ ያላቸው  ሰው በወረዳው ቦክሬ ቀበሌ ሚጽልቶ የተባለው አነስተኛ ወንዝ በደራሽ ውሃ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ ተወስደው ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡ እየጣለ ባለው ከባድ  ዝናብ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነዋሪዎች በጎርፍና ናዳ ምክንያት መፈናቀላቸውን ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው  በማሳ ላይ የነበረ ሰሊጥና በቆሎ ሰብል ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል። በወረዳው ያሉ 11 ቀበሌዎች በጎርፍ መከበባቸውን ጠቁመው ነዋሪዎቹን ወደ ሌላ አካባቢ ለማዛወር የተደረገው ሙከራ በዝናቡ ከባድ መሆን  አለመሳካቱን አመልክተዋል። አምና በአካባቢው በተፈጠረ ተመሳሳይ ችግር የ40 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስተዳዳሪው አስታውሰው  "የአሁኑ ችግር ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ድጋፍ ያስፈልገናል" ብለዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ  ማዶሬ ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ በሰጡት ምላሽ የዞኑ አስተዳደር ለተጎጂ ቤተሰቦች ድጋፍ የሚያደርግ ኮሚቴ ወደ ስፍራው ለመላክ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል። በአካባቢው በሚቀጥሉት ቀናትም የዝናቡ መጠን ሊጨምር እንደሚችል የሚትሮሎጂ ትንበያ እንደሚጠቁም አቶ አለማየሁ ገልጸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል። የደቡብ ህዝቦች ክልል አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በክልሉ  የተለያዩ አካባቢዎች ሊከሰት የሚችለውን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከልና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችም መልሶ ለማቋቋም ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም