ፓርቲዎቹ ኢጋድ ያቀረበውን የሰላም ምክረ ኃሳብ ተቀብለው ተግባራዊ እዲያደርጉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች በቅርቡ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የቀረበውን የሰላም ምክረ ኃሳብ ተቀብለው ተግባራዊ እዲያደርጉ ተጠየቀ። የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ላይ ለመምከር ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተሰብስቧል። ከሶስት ዓመታት በፊት በደቡብ ሱዳን ሁለቱ ጎራዎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ዳግም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው። በዚህም በዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት፣ ሁሉን ዓቀፍ የሰላም ስምምነትና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ማስቀመጥ በሚሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ከታጠቁና ካልታጠቁ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ምክክር ማድረጉን የምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ ኤስ ፒ ኤል ኤም በሚል ጣምራ ግንባር ከፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ እና የሽግግር መንግሥት አባላት ጋርም  መወያየቱንም ዶክተር ወርቅነህ አመልክተዋል። በዚህም በፖለቲካ ቡድኖቹ መካከል ጥላቻና ቁርሾ እንዲቆም፤ ይህንንም በተላለፉ አካላት ላይ የሚወሰደውን ሕጋዊ እርምጃ በተመለከተ ውይይቱ እንደ አዲስ እንዲሄካድ ተደርጓል ብለዋል። ይሁን እንጂ በፓርቲዎቹ መካከል ያለው አለመተማመንና አለመግባባት የሰላም ስምምነቱን እያደናቀፈው መሆኑን ነው ዶክተር ወርቅነህ የገለጹት። ይህንንም ተከትሎ ኢጋድ የሰላም ድርድሩን ተግባራዊ ለማድረግና የሚፈለገውን የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ያለውን ምክረ-ሀሳብ ለደቡብ ሱዳን ፓርቲዎች ማቅረቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። በኢጋድ የቀረበው የሰላም አማራጭ ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ያስገባ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ሕግ ተላላፊዎችን ለመቅጣትም ኢጋድ አጽንዖት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። "አሁን ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን" ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በኢጋድ በቅርቡ የቀረበውን የሰላም ድርድር ምክረ ሀሳብ በአግባቡ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። ከዚሁ ጋርም ፓርቲዎቹ በሀገሪቱ የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ባለፈው ታህሳስ 2010 የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉም ዶክተር ወርቅነህ ጠይቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ አክለውም፤ "በኢጋድ የቀረበውን ምክረ-ሀሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ በስቃይ ላይ የሚገኙትን ደቡብ ሱዳናውያን መታደግ ይገባል፤" ብለዋል። የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ ሕግ በሚጥሱ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል አጥፊዎቹ እንዲተላለፉለት ኢጋድ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም እስካሁን ምንም ምላሽ እንዳልተገኘ ጨምረው አስታውቀዋል። በመሆኑም በቀጣይ ኢጋድ በእነዚህ አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ዶክተር ወርቅነህ አስጠንቅቀዋል። በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በተካሄደው ልዩ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ውይይት  በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተገኙ ሲሆን በሀገሪቷ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በተመሳሳይ ገልጸዋል። ላለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከአራት ሚሊዮን የሚልቁትን ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉና ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደጎረቤት አገራት እንዲጠለሉ አስገድዷል። በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ይፋ ያደረገው መረጃ የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮችን ለመደገፍ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም