በሐረር ከተማ የሚጠበቅባቸውን ግብር ባልከፈሉ 209 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ከተማ የሚጠበቅባቸውን ግብር ባልከፈሉ 209 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
ሐረር መጋቢት 7/2011 በሐረር ከተማ የሚጠበቅባቸውን ግብር ሳይከፍሉ በተገኙ 209 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አብዱላዚዝ ሱፍያን ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት 161 ከሚሆኑ ግብር ከፋይዎች ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር፡፡
ከዚህ ወስጥ ከ276 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡንና ከንውኑም ግዴታቸውን ከተወጡ ግብር ከፋዮች የተገኘ ነው፡፡
ይህም 38 በመቶው ግብር ከፋይ ግብር ግዴታውን አለመወጣቱን የጠቆሙት አቶ አብዱላዚዝ ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስርዓት ለማስያዝ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ስድስት ወረዳዎች ለሶስት ቀናት በተደረገው እንቅስቃሴ ግብር ሳይፈሉ የንግድ ስራ ያከናወኑ የነበሩ 209 የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ መደረጉን አስታውቀዋል።
ከታሸጉት የንግድ ተቋማት መካከል የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ሆቴል፣ የእህል መጋዘን እና የኤሌክተሮኒክስ እቃዎች መሸጫ ይገኙበታል፡፡
ተቋማቱ ግብር የመክፈል ግዴታቸውን በመወጣት ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የክልሉ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብዲ ሳኒ በበኩላቸው 17 ደንብ አስከባሪዎች ከግብረ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
ለከተማው ነዋሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በመከናወናቸው ለግብረ ኃይሉ ስራ አጋዥ በመሆን ድጋፍ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡
በሐረር ከተማ በተለምዶ ሸንኮር በተባለው አካባቢ በእህል ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ደመና ዘሪሁን ገበያ በማጣታቸው ግብራቸውን በወቅቱ መክፈል እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
የእህል መጋዝናቸው በግብረ ኃይሉ መታሸጉን የገለጹት አቶ ደመና "የደረጃ 'ሀ' ግብር ከፋይ በመሆኔ ገቢዬ ታይቶ ግብር እንድከፍል ይደረግልኝ" ብለዋል።
ግብረ ኃይሉ በቀጣይ 60 ቀናት ውስጥ ግብር የማይከፍሉትን በመለየት ስርዓት የሚያሲያዙ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥሉም ተገልጿል፡፡